የከፍተኛ ፍርድ ቤት በኢሕአፓ አመራሮች የዋስትና ጥያቄ እና የፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ላይ ነገ ውሳኔ… — Addis Maleda - አዲስ ማለዳ — TG.ME

Addis Maleda - አዲስ ማለዳPhoto
የከፍተኛ ፍርድ ቤት በኢሕአፓ አመራሮች የዋስትና ጥያቄ እና የፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ላይ ነገ ውሳኔ እንደሚሰጥ ጠበቃቸው ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 28  ቀን 2018 ዓ.ም (#አዲስ_ማለዳ)

በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ በሚገኙት የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)አመራሮች እና አባላት የዋስትና መብት፣ እንዲሁም ፖሊስ ባቀረበው ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ጥያቄ ላይ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነገ ነሐሴ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ውሳኔ እንደሚሰጥ የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ዛሬ በዋለው ችሎት፤ የፖሊስ የምርመራ ቡድን ከፎረንሲክ እና ቴክኒክ ምርመራዎች ጋር የተያያዙ ውጤቶችን ለማጠናከር፣ ተጨማሪ ምስክሮችን ለመቀበል እና የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶችን በኤግዚቢትነት ለመያዝ በሚል ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢለቀቁ ምስክሮችን ሊደልሉ ወይም ከሀገር ሊሸሹ ይችላሉ የሚል ስጋት ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።

በሌላ በኩል የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ በሰጡት ምላሽ፣ ፖሊስ ከዚህ ቀደም የቴክኒክ እና የፎረንሲክ ምርመራ ውጤቶችን አቅርቦ በቂ ማስረጃ የተሰበሰበ በመሆኑ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንደማያስፈልገው ተከራክረዋል።

ከሀገር ሊሸሹ ይችላሉ የሚለውን የፖሊስ ስጋት በተመለከተም ተጠርጣሪ አበበ አካሉ ፓስፖርት የሌላቸው መሆኑን፣ ሌሎች ፓስፖርት ያላቸው ቢኖሩ እንኳ ለኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ማሳወቅ እንደሚቻል በመግለጽ ተጠርጣሪዎቹ በዋስትና እንዲለቀቁ ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱ የሁለቱንም ወገን ክርክር ካዳመጠ በኋላ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናት መፍቀድ እና ለተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብት መስጠት በሚለው ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለነገ ቀጠሮ ሰጥቷል።


ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦

YouTube ➲ t.ly/vSgS
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
Twitter ➲ t.ly/mxA
Telegram
Addis Maleda - አዲስ ማለዳ
ዜና ከምንጩ
👍1
September 3, 2026 2.9K 1 4