የነዳጅ ዋጋ እንደ አዲስ ባገረሸው የመካከለኛው ምስራቅ ግጭት በቀን ከአራት ዶላር በላይ ጨመረ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 27 ቀን 2018 ዓ.ም (#አዲስ_ማለዳ)
በአሜሪካና በኢራን መካከል ግጭት እንደገና በመቀስቀሱ ምክንያት በመካከለኛው ምሥራቅ የነዳጅ አቅርቦት ሊስተጓጎል ይችላል የሚል ስጋት እያየለ በመምጣቱ የነዳጅ ዋጋ በትናንትናው ዕለት በአንድ በርሜል ከአራት ዶላር በላይ ጨምሯል።
ይህም በአምስት ሳምንታት ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ ላይ እንደደረሰ ተሰምቷል።
ጭማሪውም በብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ላይ 4.6 በመቶ እንድጨምር አድርጎ የአንድ በርሜል ዋጋ 94.65 ዶላር ሆኗል ።
በተመሳሳይ የአሜሪካው ዌስት ቴክሳስ ኢንተርሚዲየት የነዳጅ ዋጋ ደግሞ 4.46 ዶላር ወይም 5.2 በመቶ ጨምሮ፣ በአንድ በርሜል 90.22 ዶላር ላይ እንደደረሰ ሮይተስ ዘግቧል ።
አሜሪካ በኢራን ውስጥ ባሉ ዒላማዎች ላይ አዳዲስ የአየር ጥቃቶችን መፈጸሟን የገለፀች ሲሆን ይህም ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተካሄደው የጥቃት ልውውጥ ወደ ሰፊ ግጭት ሊሸጋገር ይችላል የሚለውን ተስፋ አጨልሟል።
የነዳጅ ዋጋ ግጭቱ እንድጨምር ቢያደርገውም ከግጭቱ በፊት በሆርሙዝ ባሕረ ሰላጤ ሲያልፉ የነበሩ ሁለት የነዳጅ ማጓጓዣ መርከቦች መጎዳታቸው መዘገቡ የነዳጅ ገበያውን ስጋት እንዳባባሰው ተጠቁሟል።
የሆርሙዝ ባሕረ ሰላጤ ለዓለም የነዳጅ አቅርቦት ወሳኝ የባሕር መንገድ ቢሆንም ፣ ኢራን በአሁኑ ወቅት ለንግድ መርከቦች መንገዱን ዘግታለች።
ቴህራን በበኩሏ የነዳጅ ምርቶች ከባሕረ ሰላጤው እንዳይላኩ እንደምታደርግ በማስጠንቀቅ አቋሟን አጠናክራ ቀጥላለች።
ይህ የሆነው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ጥቃቶቿ ከቀጠለች “በከፍተኛ ኃይል” ተጠቅመው እንደሚመቷት ካስጠነቀቁ በኋላ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም የአሜሪካው የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሴንትም ዋሽንግተን አዳዲስ ማዕቀቦችን ለመጣል መዘጋጀቷን ተናግረዋል።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፁ ላይ ባሰራጨው መልዕክት፣ የአሜሪካ ጦር በኢራን ውስጥ በሚገኙ የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ዒላማዎች ላይ ጥቃት መጀመሩን ገልጿል።
ይህም ጥቃት የተፈጸመው ኢራን በባሕረ ሰላጤው ውስጥ በንግድ መርከቦችና በአሜሪካ ወታደሮች ላይ ጥቃት ለመፈጸም ከሞከረች በኋላ መሆኑን ዕዙ አስታውቋል።
በዓለም ዙሪያ በነዳጅ ማጣሪያ ተቋማት ላይ የተፈጠሩ መስተጓጎሎች፣ በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅና በሩሲያ ያሉ ተቋማት ላይ በተፈጠሩት ክስተቶች የናፍጣ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ሆኗል ።
ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
Twitter ➲ t.ly/mxA
Telegram
Addis Maleda - አዲስ ማለዳ
ዜና ከምንጩ

6September 2, 2026 3.3K 3