በኡጋንዳ የኢቦላ ወረርሽኝ ማብቃቱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ ሐሙስ፣ ነሐሴ 21 ቀን 2018 ዓ.ም… — Addis Maleda - አዲስ ማለዳ — TG.ME

Addis Maleda - አዲስ ማለዳPhoto
በኡጋንዳ የኢቦላ ወረርሽኝ ማብቃቱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 21 ቀን 2018 ዓ.ም (#አዲስ_ማለዳ)

በኡጋንዳ ተከሰቶ የነበረው የቡንዲቡግዮ የኢቦላ ዝርያ ወረርሽኝ መጠናቀቁን፤ በአንጻሩ በአጎራባች ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ የቫይረሱ ስርጭት አሁንም በቁጥጥር ሥር አለመዋሉን የዓለም ጤና ድርጅት ባለሥልጣን አስታወቁ።

ለኡጋንዳ የተሰጠው ከበሽታው ነፃ የመሆን ማረጋገጫ፣ የሃገሪቱ መንግሥት እ.አ.አ ሐምሌ 28 ያቀረበውን ጥሪ ተከተሎ የመጣ ሲሆን፣ በኡጋንዳ በወረርሽኙ 20 ሰዎች ሲያዙ የሁለት ሰዎች ሕይወት አልፏል። የዓለም ጤና ድርጅትም ምንም ዓይነት የቫይረሱ መተላለፊያ ሰንሰለት አለመቀረቱን ለማረጋገጥ እስከዚህ ሳምንት ድረስ ሁኔታውን ሲከታተል መቆየቱን ገልጿል።

ነገር ግን የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ክልል ድንገተኛ ዝግጅት ዳይሬክተር ዶክተር ማሪ ሮዝሊን ቤሊዛየር በድርጅቱ ቀጣናዊ ስብሰባ ወቅት እንደገለጹት፣ በዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተወሰኑ መሻሻሎች ቢኖሩም የበሽታው ስርጭት እየጨመረ ይገኛል። በኮንጎ የተከሰተው ይህ ወረርሽኝ በታሪክ ሁለተኛው ከፍተኛ ገዳይ ሲሆን የመከላከል ጥረቱንም ፈተና ላይ ጥሎታል።

በኮንጎ መንግሥት መረጃ መሠረት እስከ ማክሰኞ ድረስ ከ2,700 በላይ ሰዎች ሲሞቱ ከ5,600 በላይ ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል።
የበሽታው የመተላለፍ ሁኔታ አሁንም ከፍተኛ ነው ያሉት ዶክተር ማሪ፤ የስርጭቱን ፍጥነት ማዘገየት ብንችልም አሁንም አቅጣጫውን ሙሉ በሙሉ መቀየር አልቻልንም ብለዋል።

አክለውም በተጋላጭ ሰዎች ፍለጋና በምርመራ ሂደት ላይ መሻሻሎች መኖራቸውን ጠቁመው፣ የቡንዲቡግዮ ቫይረስ በፍጥነት ቢስፋፋም እስካሁን ምንም ዓይነት የዝርያ ለውጥ አለማሳየቱን ገልጸዋል።

ይህን የምሥራች ቢያበስሩም፣ በኮንጎ በጣም በተጎዱ አካባቢዎች የሕክምና እና የግል መከላከያ መሣሪያዎችን ለማቅረብ ለሚደረገው የሎጀስቲክስ ሥራ አፋጣኝ የ30 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ እጥረት እንዳለ አስጠንቅቀዋል። ያለዚህ አፋጣኝ ኢንቨስትመንት ያገኘነውን ግስጋሴ የማጣት አደጋ ላይ እንወድቃለን ሲሉ ዶክተር ማሪ አሳስበዋል።

ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦

YouTube ➲ t.ly/vSgS
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
Twitter ➲ t.ly/mxA
Telegram
Addis Maleda - አዲስ ማለዳ
ዜና ከምንጩ
❤11🙏4
August 27, 2026 5.1K 1 6