የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ሀገራዊ የምክክር ጉበኤው በብልጽግና ፓርቲ ዘዋሪነት ስለተቋጨ ምንም ዓይነት እውቅና አልሰጥም አለ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 26 ቀን 2018 ዓ.ም (#አዲስ_ማለዳ)
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፤ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤውን በብልጽግና ፓርቲ ዘዋሪነት የተከናወነ፣ ነጻ እና ገለልተኛ ባለመሆኑ ምንም ዓይነት እውቅና አልሰጥም፤ እንዲሁም ሀገሪቱ በገዢው ፓርቲ መር በሆነ ጦርነት እየወደመች የምትገኝበት ወቅት የተካሄደ ነው ሲል ኮነነ።
ፓርቲው “በብልጽግና መሪነት የተካሄደ” ነው ያለው የሀገራዊ ምክክር ሂደትና አጀንዳዎች፤ ወገንተኝነት ያበዛበት፣ ገዥው ፓርቲ ስልጣኑን ለማራዘም የተጠቀመበትና ነጻ ያልሆነ በመሆኑ እውቅና እንደማይሰጠውና ተቀባይነትም እንደሌለው በዛሬው ዕለት ባወጣው ወቅታዊ መግለጫ አስታውቋል።
አዲስ ማለዳ የተመለከተችው መግለጫ፤ ፓርቲው ጦርነትና የኢኮኖሚ ውድቀት እየተባባሰ እንደሄድ አንስቷል። ፓርቲው መንግሥት የፖለቲካ ጥያቄዎችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ “በጦርነት ይዋጣልን” በማለቱ ሀገሪቱ ለአውዳሚ ጦርነቶች፣ ለዜጎች መፈናቀል፣ ለእስራትና ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ውድቀት ተዳርጋለች ብሏል። አክሎም “ጦርነት አልበቃ ያለው አንባገነን ስርኣት” የሚለው ፓርቲው ማንነት ተኮር እስር፣ የኢኮኖሚ መንኮታኮት፣ መፈናቀል፣ እገታ እንዲሁም “ሀገር አልባነት” የኢትዮጵያውያን ዜጎች የእለት ለእለት ኑሮ እየሆነ ነው ብሏል።
የሀገራዊ ምክክር ዓላማን ያብራራው ፓርቲው “የገዥውን ኃይል አቋም ማጠናከር ሳይሆን የሀገሪቱን ጥልቅ ፖለቲካዊ ችግሮች በእኩልነት ማየትና ዘላቂ መፍትሔ መፈለግ ነው።” ነው ሲልም አመልክቷል።
ፓርቲው በመግለጫው ገዥው ብልጽግና ፓርቲን በብዙ ጉዳዮች ኮንኗል። ከዚህም ዉስጥ “በብልጽግና መር ጦርነቶች” ሀገር እየወደመች ነው ያለ ሲሆን ሌላው ደግሞ ምክክሩን የእሱን ስልጣን ለማራዘም እየተጠቀመበት እንደሆነ ጠቁሟል።
አክሎም ገዥው ፓርቲ የኢትዮጵያ ልሂቃንን የሚያለያዩ በበቂ ውይይት ያልተደረገባቸውና ስምምነት ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች ለውይይት ማማጣቱ እና በአራት ሳምንት “ስብሰባው” አጀንዳ ብሎ ማምጣቱ ልክ እንዳልሆነ ጠቅሷል። እነዚህ ጉዳዮች ከህገ መንግስት ጉዳይ፤ የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጉዳይ፤ የክልሎች አከላለል እና የወሰን ጉዳዮች፤ የብሔራዊ መግባቢያ ጉዳይን ማምጣት አንዱን ወገን በመደገፍ ሌላውን በመቃወም እንዲሁም በሊህቃኑ መካከል ገና “ያልሰከኑ የውይይት ርዕሶችን እንደገና መነታረኪያና መከፋፈያው ለማድረግ” ታትሯል ሲል ኮንኗል።
የአዲስ አበባ ጉዳይ በተመለተ ደግሞ የአርሶ አደሩን መሬት በህገወጥ መነገድ ሽጦ እና በሙስና ከተዘፈቀ በኋላ ከሳሽ ሁኖ መጥቷል ያለ ሲሆን፣ በብልጽግና የተመራ የህዝብ መፈናቀል በማድረግ እንዲሁም የእምነት ቦታዎችን ጭምር በማፍረስ በህዝብ ላይ “ወንጀል ሰርቷል” ብሏል።
የኮሪደር ልማትና “ሸገር ከተማ” በሚል ስም የተከናወኑት ተግባራት ህገ-ወጥ ማፈናቀልን ጨምሮ የተወላጅ እና ነዋሪዎችን መብት ገፍፏል ሲል የሚከስሰው ፓርቲው፣ በሸገር ከተማ ደግም ያለአግባብ የተጫኑ የተለያዩ መዋጮዎችን ተጥሎባቸዋል ሲል ኮንኗል።
ፓርቲው ከከተማው ተፈናቅለው ወደ አዲሱ መኖሪያቸው ሲደርሱ ለሚሊሻ፣ ለኦሮሚያ ልማት ማህበር፣ ለኮብልስቶን፣ ለግድግዳ ጌጥ፣ ቀለም መቀቢያ፣ ለዞን ጽህፈት ቤት ማስገንቢያ፣ ለግቢ ቴራዞና ለብሎክ ካሜራ ማስገቢያ የሚሉ መዋጮዎች እንደሚጠብቃቸው አንስቷል።
በፍትሐዊነት ሽፋን በሚደረጉ የብሔር ምደባዎች፤ ማለትም ኮታዎች ምክንያት ሙያተኞች ተገፍተው በፖለቲካ ታማኝነትና ዘውገኝነት ላይ የተመሰረተ አሰራር በመስፋፋቱ ማህበረሰባዊ መራራቅና የትርክት ልዩነቶች እንዲፈጠሩ ተደርጓል ብሏል። አክሎም ለፓርቲው ቤተሰብ ያልሆኑ ባለሃብቶችም ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል።
በድሬዳዋ ከተማ ሰፊውን ህዝብ ከፖለቲካ ተሳትፎ ያገለለና በዘውግ ከፍሎ በመቶኛ ያካፈለ “አፓርታይደዊ ህግ” ሲል በጠራው አሰራር ከመሻሻል ይልቅ ይህ ምክክር ተጨማሪ ቀውሶችን ለመፍጠር የተሰየመ ነው በሚል ኮንኗል።
በሁሉም ባለድርሻ አካላትና በህዝብ ዘንድ ከምስረታው ጀምሮ ተቀባይነት ያለው፣ አካታች፣ ከወገንተኝነት የጸዳና በነጻነት የሚሰራ እውነተኛ ሀገራዊ የምክክርና ብሔራዊ እርቅ እንዲካሄድ ጥሪ አቅርቧል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በምክክር ጉባኤው ሲካሄድም ከዚያ ቀደም በሚሰጣቸው መግለጫዎች ላይ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው አካታች እና አስታፊ እንዲሁም ገለልተኛ እንደሆነ በተደጋጋሚ መግለፁ የሚታወስ ነው።
ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
Twitter ➲ t.ly/mxA
Telegram
Addis Maleda - አዲስ ማለዳ
ዜና ከምንጩ

11
5
1September 1, 2026 2.5K 8