ለሙስሊሞች ትልቁ ጠላት የውጭ ወራሪዎች ወይንም ጥቃት አይደለም። የኢስላም ትልቁ ጠላት ፅንፈኝነት ነው። አክፋሪነት ! ከኔ ውጭ ትክክለኛ ሙስሊም የለም ማለት!
ፅንፈኝነት ወይንም ተክፊርነት በሙስሊሞች ያመጣውን ውድመት ማንም አላመጣውም!
የመጀመሪያውን ትልቁን የሙስሊሞች ፊትና የፈጠረው ተክፊርነት ነው።
ታላቁን ሶሀባና ኸሊፋ ኡስማንን ትክክለኛ ሙስሊም አይደለህም ሙብተዲእ ነህ ብለው ገደሏቸው። ሹፉ ከኡስማን በላይ እነርሱ ትክክለኛ ሙስሊም ሆነው አመፁባቸው። እና ያ ፈተና በኢስላም ታሪክ እስካሁንም ጠባሳውን ያላነሳውን የመከራ የመፈራረቅ ጥንስስ ጠንስሶ አለፈ።
ከዚያ በሗላ ወልዩሏህ አሊ ላይ ትክክለኛ ሙስሊም አይደለህም ብለው አመፁባቸው። አላህ ያሳያችሁ ከአሊ በፊትኮ ኢስላምን የተቀበለ አንዲም ወንድ አልነበረም። ከህፃንነቱ እስከ እለተ ሞቱ አንድም ቀን ሳያዛንፍ የረሱሉ ሶለሏሁ አለይሂ ወሰለም ክንድ ሆኖ ከበድር እርከ ኸይበር ሰንደቃቸውን ተሸክሞ ፤ ከየመን እስከ ኩፋ ኢስላምን ዘርቶ እኔ ወልይ የሆንኳችሁ ከዚህ በሗላ ወልያችሁ አልይ ነው ያሉትን ሰው በረሱሉ አንደበት ሁሉም ሰው ጀነትን ሲናፍቅ ጀነት ግን አልይን አማርን ቢላልን ትናፍቃለች ያሉትን ሰው ከአላህ መንገድ ወጥተሀል ብለው ሱብሂን ሊሰግድ በሄዱበት ታላቁ አሊ ተገደሉ።
ያ ፈተና ዛሬ ላይ ላለው የሱኒ-ሺአ ስንጥቅ መሰረቱን ያደላደለ ፤ ለኡመውይ አባሲዮች መተላለቅ በሩን የበረገደ ፤ አሁን ላይ ያሉ ፊርቃዎች ስራቸውን የሚመዙለት ትልቅ ጠባሳን ጥሎ አለፈ። ያ ታሪክ ያደረሰውን ፈተና የሞንጎል ወራሪዎችም ሆነ የመስቀል ጦረኞች አላደረሱትም። ምክንያቱም የነርሱ ጭፍጨፋና ወረራ እዚያው የቆመ ሲሆን ይህ ግን ወደፊትም የሚቀጥልን የፈተና ስር የተከለ ነው።
ከዚያ በሗላ በርካታ ፅንፈኞች ወጥተው የፈተናውን አዲማስ እያሰፉ እያወሳሰቡ ተደማምረው ተደማምረው ዛሬ ሙስሊሙ አለም ላለበት ውድቀት አድርሰውናል።
እስኪ መካከለኛው ምስራቅ ላይ ያሉ መስጅድ የሚያጋዩ ፤ ቦምብ ታጥቀው የሚያፈነዱ ፤ አሏሁ አክበር እያሉ በአደባባይ ላይ ሰው የሚያርዱ ጨካኞችን እይዋቸው። ሙስሊም ያልሆኑ ህዝቦች ኢስላም ሲባል ያ ምስል ቀድሞ እንዲጋረጥባቸው በማድረግ በኩል እነርሱ የተወጡት ሚና ከሁሉም ይከፋል። እርግጥ ነው ምእራባውያን በእጅ አዙር እየዘወሩ የፈለጉትን ፅንፈኝነት ኦንደሚያስፈፅሙባቸው ይታወቃል።
እስኪ በየመሳጅዱ በየማህበራዊ ሚዲያው ኡስታዝ ነን የሚሉ ፅንፈኝነትን የሚሰብኩ ሰዎችን የሚዘሩትን ፈተና እዩት።እከሌ እንዲህ ነው አትቅረበው ፤ እከሌ እንዲህ ብሏል ከእስልምና ወጥቷል ፤ እከሌዎችን ተጠንቀቁ ከእስልምና ወጥተዋል ......ወዘተ እንደት ሁሌ እንዲህ ይሰበካል!
ከዚያ ፅንፈኝነት ደግሞ መዘዙ አንድ ቡድን ሆነው ሌሎችን ከኢስላም ሲያስወጡ የነበሩ አካላት መልሰው እየተሰነጣጠቁ እየተሰነጣጠቁ ለስምም ወደሚያስቸግሩ ክፍልፋዮች ይወርዱና የሚቀረውና የሚሰፋው ፊትናቸው ብቻ ይሆናል።
አንድ ሰው በኢስላም ማእዘናት በኢማን ማእዘናት እስካመነ ከኢስላም የማስወጣት ስልጣን ያለው አንዳች የምድር ሀይል የለም።
አቂዳ ኢስላም ነው!
መንሀጅም ኢስላም ነው!
ከቁርአንና ሀዲስ የተለየ የወጣም አቂዳ የለም። አቂዳ ቁርአን ነው ሌላ አይደለም!
አንድ ሰው በኢስላምና ኢማን ማመኛዎች ካመነ ሌላ ምን አይነት አቂዳ እንዲፈጠር ነው የሚፈለገው?
ነብያችን አለይሂ አሶላቱ ወሰላም አብረዋቸው የሚሰግዱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሙናፊቆች ነበሩ። አንዳቸውንም አክፍረው ከኢስላም ውጭ ናቸው ብለው ለሶሀቦች አልተናገሩም። ለምን?
ያንን ቢጀምሩ እኛ እርስበርሳችን እየተከፋፈርን ተዳክመን ስለምናልቅ። የፊትና በር ስለምንከፍት!
ነብያችን ሶለሏሁ አለይሂ ወሰለም ፅንፈኝነትን አውግዘዋል አስጠንቅቀዋል። " ፅንፈኞች ተጠፉ!" በማለት 3 ጊዜ ነው ደጋግመው የተናገሩት።
አንድ ሰው ላኢላሀኢለሏህ ካለ ተጠንቀቅ ! ላኢላሀኢለሏህን አንተ የምታፀድቅለትም የምትከለክለውም አይደለም። ሲጀመር ከርሱ የተለየ የመመዘንም የማፅደቅና ውድቅ የማድረግም ስልጣን የለህም። በኢስላም በኩል ያለህ ስልጣን የመመካከር ዱአ የመዳረግ የመተዛዘን ነውር የመደበቅ ስልጣን ነው። ኢማኑን መፈላፈል የሚችለው ራሱ አማኙ ብቻ ነው። የኢማን ቦታው ቀልብ ውስጥ ነችና ቀልብን ደግሞ የሚያውቃት የቀልቡ ገለባባጭ የሆነው አንድየ ነው!
ነብያችን ሶለሏሁ አለይሂ ወሰለም ለሶለቦቻቼው ሲናገሩ " ሶላታችንን የሰገደ ፤ ቂብላችንን የተቅጣጨ ፤ ከበላነው አብሮ እርዳችንን የበላ እኛ በርሱ ላይ እርሱ በኛ ላይ የኢስላም ሀቅ አለብን" ነው ያሉት። ከዚያ በታች ያለውም ሲሩን የማወቅ ስልጣን የኛ አይደለም።
ኡመር ኢብኑል ኸጧብ አላህ ስራቸውን ይውደድላቸውና እንደነገሩን " እኛ ከውጭ ባየነው ብቻ ነው የምንፈርደው ውስጥን የመመራመር ስልጣን ግን የአላህ ብቻ ኘው"
ራሳችንን ብንመረምር ዘርዝረን የማንዘልቀው ጉድና ጉዳድፍ አለብን። ምናልባት ይፋ ቢወጣ ቀና ብለን መሄድ የማያስችለን!
እና ፅንፈኝነትን እንራቅ !
እንጠንቀቅ!
ቴሌግራም
👉 t.me/Seidsocial
Telegram
Seid Social
አለም አቀፋዊ መረጃዎች ምልከታዎችና ታሪካዊ ክስተቶች ይቀርቡበታል

118
12
10
2September 5, 2026 5.5K 12 15