አዲስ ሪፖርተር - NEWS: post #30852 — TG.ME

በምሥራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ጢያ፣ ሱተን እና ኧሽከዲየ ቀበሌዎች የጸጥታ ችግር መከሰቱ ተገለጸ።

በጢያ፣ ሱተን እና ኧሽከዲየ ቀበሌዎች የጸጥታ ችግር መከሰቱን፤ በዚህም ከባድ የጦር መሣሪያ ተኩስ እንደሚሰማና ነዋሪዎች ቀያቸውን ለቀው እየሸሹ መሆኑ ከአካባቢው የደረሱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የወረዳው የጸጥታ ኃይል በአጥቂዎቹ ጫና ወደ ቡኢ ከተማ ማፈግፈጉን እና አንዳንድ ነዋሪዎችም አካባቢውን ለቀው ወደ ቡኢ ከተማ መግባታቸውን የአካባቢው ምንጮች ይገልጻሉ።

በተለይ "አቅም-አጠር አረጋውያን፣ እናቶች፣ ሕፃናትና ሕሙማን በግጭቱ መካከል ቀርተዋል" የሚል መረጃ የተሰማ ሲሆን መረጃውም ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል።

በክስተቱ እስካሁን ምን ያህል የሰው ሕይወት መጥፋቱ ወይም የደረሰውን የጉዳት መጠን ማወቅ ያልተቻለ ሲሆን ሁኔታውን በተመለከተ በይፋ የወጣ መንግሥታዊ መረጃም የለም፡፡ ሆኖም የጸጥታ ችግሩ በፍጥነት እንዲቀረፍና በአካባቢው የሚገኙ ንጹሐን ዜጎች ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ነዋሪዎች እየጠየቁ ነው፡፡

የፌዴራል መንግሥትና የክልሉ የጸጥታ ተቋማት እንዲሁም  የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ድርጅቶች በአካባቢው የሚገኙ ንጹሐንን ለመጠበቅ ፈጣን እርምጃ ይውሰዱ የሚል ጥሪም ቀርቧል።

በዚህ ቀጣና ቀደም ብሎም መሰል የጸጥታ ችግሮች ሲከሰቱ መቆየታቸው የሚታወቅ ሲሆን አሁን የተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ ችግሩ በተለያየ ጊዜና ቦታ መከሰቱን እንደቀጠለ ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡

@Addis_Reporter
@Addis_Reporter
❤16👍4🤔2😢1
August 25, 2026 4.8K 10