📚 አዳም ረታ ™: post #8377 — TG.ME

ስብሃት:-
''የሚጥል በሽታ ነበረብኝ። የእኔ እንደ ዶስቶየቪሲኪ እያነሣ የሚያፈርጥ አይነት አይደለም። እኔ ላይ የደረሰብኝን ወንድሞቼ እንደነገሩኝ ሌሊት እነሳና በኃይል! በኃይል እጮሃለሁ። ተነስቼ እሮጣለሁ። ይዘውኝ ያስተኙኛል።

ጡንቻዬ ደግሞ የዛን ጊዜ በጣም ጠንካራ ነው። ጠዋት ስነሣ በጣም ድክም ያደርገኛል። አንዳንዴም ጉንጬን እነክሳለሁ። አንዳንዴ ጧት ስነቃ ለመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሰከንዶች ማን እንደሆንኩና የት እንደሆንኩ አላውቅም። በዚህ በሽታ ምክንያት ልጅ ላለመውለድ ወስኜ ነበር።

ዘነበ ወላ : ''ለምን?''

ስብሃት : በምወልደው ልጅ ይተላለፋል የሚል እምነት ነበረኝ።

ዘነበ ወላ : ባለቤትህ በዚህ ተስማማች?''

ስብሃት : ምን አማራጭ አላት? የሚቸልኮትስ ቼርማን እንደ አባቷ ነበር። ኤውሮፓ ውስጥ ከሚገኙት አራት ዋነኛ የንዲህ አይነት በሽታዎች እስፔሻሊስት አንዱ ከሆነው ሀኪም ጋር ሚስተር ዲክ ቀጠሮ ያዘልን።

''በሽታህ በዘር አይተላለፍም'' አለን ''ነገር ግን ማንኛውም ልጅ ሲወለድ ኤፕሌፕቲክ ለመሆን ሦስት ከመቶ እድል አለው። ስለዚህ ምናልባት ያንተ ልጅ ኤፕሌፕቲክ ቢሆን፣ ሎተሪው ሦስት ከመቶው ደርሶት ነው እንጂ ካንተ ወርሶት አይደለም'' አለኝ። መድኃኒት አዘዘልኝ በቀን አንዴ ጊዜ የሚዋጡ።

''ለብላታ ደሬሳ ያመኛል ሳልላቸው ላማክራቸው ወሰንኩ። ይህ በሽታ በእኛ ሀገር <የባርያ በሽታ> ይባላል። አነሣሁና ጠየቅኳቸው። ይህንን ጥያቄ ለመመለስ እንደ ማርኮ ፖሎ ጉዞ ከአንድ ሰአት በላይ በባርያ በሽታ ትንታኔ ይዘውኝ ተጓዙ። በመጨረሻ መልሣቸው እኔ ሠርቼበት አላውቅም ሆነ። እንደኔው የሀገራችንን መድሃኒት የሚያውቅ ጓደኛዬ እገሌ እንደነገረኝ ብለው አንድ መድሃኒት ጠሩ። ተጠቀምኩባት። ብዙም ሳልቆይ ከበሽታዬ ዳንኩኝ። ኬኒኑን መዋጥ አቆምኩ። ከሃና ጋርም የመጀመሪያ ልጃችንን ያለምንም ስጋት ለመውሰድ ተስማማንን።

ዘነበ : መድሃኒቱን ብትነግረኝ

ስብሃት : ታስሬበታለሁ

ዘነበ : ለምን?

ስብሃት : ፖሊስ ተወው ብሎ

ዘነበ : በሕግ የተከለከለ ነው?

ስብሃት : ይላሉ

ዘነበ : ታዲያ አንተ በተፈጥሮህ ሕግ አክባሪ ሰው ነህ ለምን ሕገ ወጥነቱን መረጥከው?

ስብሃት : መድሐኒቴ ከሕመም ፈውሶኛል። ደስታንም ይፈጥርልኛል።

ዘነበ : መድሃኒቱን አልነገርኸኝም

ስብሃት : አንዳንዱ ሰው በሰው ሕይወት ውስጥ ገብቶ ይፈተፍታል።

ዘነበ : በምን?

ስብሃት : ደግሞ እኮ ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው ሲል ትሰማዋለህ

ዘነበ : አልገባኝም?

ስብሃት : ግን የእኔም በባሕሪዬ አደባባይ መሆን የጎዳኝ መሰለኝ

ዘነበ : አዎን እንደሀበሻ በአደባባይ ተከናንበህ ጨለማን ተገን አርገህ የልብህን መከወን

ስብሃት : እንደዛ ነው የሚደረግ፣ ሰው ምን ይለኛል እያልክ

ዘነበ : መድሃኒቱን ግን አልነገርከኝም

ስብሃት : አልነግርህም

ዘነበ : ለምን?

ስብሃት : ዘነበ አምንሃለሁ። አንተም ሌላ የምታምንም ወዳጅ አለ። ስለዚህ ትነግረውና ሳይታወቅ መድሐኒቱን ታረክሱብኛላችሁ።

(ማስታወሻ - ዘነበ ወላ)
❤23👎1
August 8, 2026 1.3K 3