በድምፅ ትዕዛዝ አልጋዎ ድረስ የሚመጣው አስገራሚው የቻይና ሮቦት መጸዳጃ ቤት! ቻይና ለአረጋውያን፣ ለአካል…

በድምፅ ትዕዛዝ  አልጋዎ ድረስ የሚመጣው
አስገራሚው የቻይና ሮቦት መጸዳጃ ቤት!

ቻይና ለአረጋውያን፣ ለአካል ጉዳተኞች እና መንቀሳቀስ ለሚቸገሩ ሰዎች ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ "ዢያኦባን" (Xiaoban) የተሰኘ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የሚሰራ ዘመናዊ ሮቦት መጸዳጃ ቤት ይፋ አደረገች።

በዘንድሮው ዓመት በዩባን ኩባንያ የተሰራው ይህ መሣሪያ፣ እንደተለመዱት ተንቀሳቃሽ መጸዳጃ ቤቶች ሰው መግፋት ሳያስፈልገው በድምፅ ትዕዛዝ ወይም በሪሞት ኮንትሮል ሲጠራ  ወደ ተጠቃሚው አልጋ አጠገብ ይመጣል። በቤት ውስጥ ያሉ እቃዎችን ሳይጋጭ በጥንቃቄ እንዲጓዝ የሚያደርጉ ዘመናዊ ሴንሰሮችም ተገጥመውለታል።

ይህ አስደናቂ ሮቦት መጸዳጃ ቤት በሙቅ ውሃ የማጠብ፣ በሞቀ አየር የማድረቅ፣ እንዲሁም ጀርሞችን በጨረር የማምከን ችሎታ አለው። ከዚህም በተጨማሪ  መጥፎ ሽታን ሙሉ በሙሉ የሚያጠፋ ልዩ የአረፋ እና የካርቦን ማጣሪያ ቴክኖሎጂ የተካተተበት ሲሆን፣ ተጠቃሚው ሲጨርስም በራሱ ተመልሶ ወደ መቆሚያው በመሄድ ቆሻሻውን ያስወግዳል፣ እራሱን ያጸዳል፣ ባትሪውንም ቻርጅ ያደርጋል።

ይህ አዲስ ፈጠራ የዕለት ተዕለት እገዛ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች የሌላ ሰው እጅ ሳይጠብቁ ራሳቸውን እንዲችሉ ትልቅ ነፃነት ይሰጣቸዋል። በተጨማሪም በቤት ውስጥም ሆነ በአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋማት የሚሰሩ አስታማሚዎችን ከፍተኛ የስራ ጫና እና ድካም በእጅጉ የሚቀንስ ታላቅ የቴክኖሎጂ ውጤት ነው።
November 22, 2026 200