NewsAlert #Tigray #Afar " ኃላቀሩ ቡድን የፌደራል መንግስትን ወደ ግጭት ለማስገባት በዓፋር… — Gion Media — TG.ME

#NewsAlert
#Tigray #Afar

" ኃላቀሩ ቡድን የፌደራል መንግስትን ወደ ግጭት ለማስገባት በዓፋር በኩል ትንኮሳዎች ፈፅሟል ይህንንም የአዛዡና ጌታውን ሻዕብያ አጀንዳ ለማስፈፀም የተደረገ ነው " - አቶ ጌታቸው ረዳ

ጥቂት የትግራይ ኃይል አመራሮች በሻዕብያ ትእዛዝ ሰጪነት በፌደራል መንግስት ላይ ትንኮሳ እንደጀመሩና ይህን ትንኮሳ እንዲያቆሙ አቶ ጌታቸው ረዳ አሳሰቡ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚንስትር አቶ ጌታቸው ረዳ  ፤ " ፍስሃ ማንጁስና ዮሃንስ መዲድ የተባለችሁ የትግራይ ሰራዊት አመራሮች የጀመራችሁትን የግጭት ቀስቃስ እንቅስቃሴ አቁሙ " ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ሚንስትሩ " ኃላቀር ቡድን " ሲሉ የጠቀሱት የህወሓት አመራር የፕሪቶሪያ ስምምነት ለመቅደድ ሁሉም ዓይነት ትንኮሳ ቢፈፅምም የፌደራል መንግስት የአፀፋ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል ብለዋል።

" ኃላቀር " ያሉት የህወሓት አመራር ቡድን የፌደራል መንግስትን ወደ ግጭት ለማስገባት " በዓፋር በኩል ትንኮሳዎች ፈፅሟል ይህንንም የአዛዡና ጌታውን ሻዕብያ አጀንዳ ለማስፈፀም የተደረገ ነው " ሲሉ ገልጸዋል።

በዓፋር ክልል በኩል በፌደራል መንግስት ላይ የተደረገው ትንኮሳ " ጀነራል ፍስሃ ማንጁስና  ጀነራል ዮሃንስ መዲድ ናቸው የመሩት ማቆም ያለባቸው እነሱ ናቸው " ሲሉ አሳስበዋል።

" ጦር አውርድ በሚል ፀሎት በራስ ህዝብ ላይ መከራና ጭፍጨፋ መጋበዝ ክህደት ነው " ያሉት ሚንስተር ጌታቸው " በትግራይና በዓፋር በኩል ያላችሁት የትግራይ ሰራዊት (TDF ) እና የትግራይ የሰላም ሃይል (TPF) የሻዕብያን ፍላጎት ለማሳካት ወደ እርስ በርስ ግጭት መግባት የለባችሁም " ብለዋል።

" ለትግራይ የሚያስብና እርባና ያለው ሰው ሦስተኛ ዓመቱ ያስቆጠረውን የፕሪቶሪያ ውል ከወዴት ደረሰ ? ብሎ መጠየቅ ብቻ ነው የሚያዋጣው " ሲሉ አቶ ጌታቸው ረዳ ገልጸዋል።

ትላንት ማክሰኞ ጥቅምት 25 /2018 ዓ.ም ከሰዓት በኃላ በትግራይ ኃይሎች እና በትግራይና ዓፋር ክልል አዋሳኝ በሚገኙት ራሳቸውን " የትግራይ የሰላም ኃይል ታጣቂዎች (TPF) " ብለው በሚጠሩት መካካል ግጭት መቀስቀሱ በማህበራዊ የትስስር ገፆች በስፋት ተነግሯል።
#gion media
🥰1
November 6, 2025 738 1