ወደ ወልቂጤ ከተማ የሚደረግ ህገወጥ የሰዎች ዝዉዉር መበራከቱ ተገለፀ
ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ የመጣዉን ህገወጥ የሰዎች ዝዉዉርን ለመከላከል እየሰራ መሆኑን የወልቂጤ ከተማ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ፅህፈት ቤት አስታውቋል ።የፅህፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ አምርያ ከድር ለብስራት ሬዲዮ እንደተናገሩት ወልቂጤ ከተማ እንደ መሸጋገሪያነት አገልግሎት ስለምትሰጥ ከሀዲያ እና ወላይታን ጨምሮ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ወደ ከተማዋ የሚደረጉ ህገወጥ የሰዎች ዝዉዉር ተበራክቷል ።
በዚህም በዋነኝነት ተጠቂ የሆኑት ሴቶችና ህፃናት መሆናቸዉን የገለፁት ኃላፊዋ በህገወጥ ደላሎች አማካኝነት ከተለያዩ አከባቢዎች ወደ ወልቂጤ ከተማ በማምጣት እዛዉ ከተማዋ ዉስጥ እንዲሁም ወደ አዲስ አበባ እና ወደ አረብ ሀገራት በመላክ ለጉልበት ብዝበዛ ተጋላጭ እንዲሆኑ መደረጋቸውን ነግረዉናል ።እነዚህ ህገወጥ ደላሎች ህብረተሰቡ ዉስጥ ያሉ በመሆናቸዉ ባለፉት አራት ዉስጥ በተለያዩ ጊዜያት ህብረተሰቡ ጥቆማ እንዲሰጥ እና የችግሩን አስከፊነት ለማስገንዘብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ሲሰራ መቆየቱ ተገልጿል ።
እርምጃ የተወሰደባቸዉ ደላሎች መኖራቸዉን ለጣቢያችን የተናገሩት ኃላፊዋ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉ ሲሆን ህፃናቱን ወደ ቤተሰቦቻቸዉ የመመለስ ስራ ፅህፈት ቤቱ እንደሚሰራ አንስተዋል ።ወደ ዉጪ ሀገራት የሚደረግ ህገወጥ የሰዎች ዝዉዉር ዜጎች ሀብት ንብረታቸውን አለፍ ብሎም ህይወታቸዉን እንዲያጡ ምክንያት በመሆኑ ሀገር ዉስጥ ባሉት የስራ ዕድሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስገዳጅ ከሆነም በህጋዊ መንገድ ለሚሆዱበት ሀገር የማያስፈልጋቸዉን ተገቢ ክህሎት ይዘዉ እንዲሆዱ ፅህፈት ቤቱ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል ።
#gion@yegion
5November 17, 2025 929