ፍልሰታ ለማርያም ፪
የምስጋና በአል
ማርያም በሃገራችን፣ በብዙ ሁኔታዎች የምትጠቀስ ናት።
በሃዘን ማርያም ታፅናችሁ እንላለን፦ በአንድ ወቅት አንድ እናት ወጣት ልጃቸው በመሞቱ ምክንያት መፅናናት አልቻሉ፣ ዘወትር ያለቅሳሉ ይቆዝማሉ፣ በሀዘናቸው ጊዜ ብዙ እናቶች ማርያም ታፅናናሽ እያሉ እንደ ባህሉ ቢያፅናኗቸውም ሊፅናኑ አልቻሉም።
ቤተሰብ ግራ ተጋባና ካህን ወደ ቤት ጋበዙ፣ ካህኑም "አንቺ ሌሎች ልጆች አሉሽ፣ እመቤታችን ግን የነበራት አንድ ልጅ ብቻ ነበር፣ እሱንም ያለበደሉ ገደሉባት፣ እሷ ግን በአምላኳ የታመነች በመሆኗ በሀዘን አልተሰበረችም፣ እኛም እሷን ጠርተን አፅናንተንሽ ነበር፣ ልብሽን አታደንድኚ ተፅናኚ" አሉ። እኒህ እናት ወድያው ተፅናንተው ልብሳቸውን ቀይረው ለምስጋና ወደ ቤተክርስትያን ሲሄዱ እኔ ምስክር ነበርኩ።
በደስታ ማርያም በሽልም ታውጣሽ እንላለን፦ እናቶች ሲወልዱ ጥየቃ የሚሄዱ ሁሉ በማርያም ስም ይመርቃሉ፣ ከቤት ሲወጡም "ማርያም በሽልም ታውጣሽ" ብለው ይወጣሉ።
ማርያም አምላክ የሆነ ልጇን ስትወልድ ሴቶች የሚያዩትን ወግ አላየችም፣ ቦታ አልነበረምና በበረት ወለደችው፣ ነገር ግን ልጇን የወለደችበት በረት ወድያው ተቀየረ፣ ከሩቅ ሀገር የመጡ ጠቢባን ወርቅ አመጡ፣ የወለደችበትን ስፍራ በከርቤ አጠኑት። በእጣን መአዛ በረቱን ቤተ መቅደስ አስመሰሉት፣ ማርያም የወለደችው በረከት ነውና በረቱን መቅደስና ቤተ መንግስትም አስመሰለችው።
በካቶሊካውያን፣ በምስራቃውያንና በኦሬንታል ኦርቶዶክስ፣ በወንጌላውያን፣ በሉተራን፣ በሪፎርሚስቶች፣ በአንጀሊካን፣ በሜቶዲስቶች እና በመጥምቃውያን አመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የኢየሱስ እናት መሆኗ ይታወቃል፣ "እመ አምላክ" መሆኗ ይታወቃል። በቁራን ውስጥም ብዙ ጊዜ ከመጠቀሷም በላይ አንድ ሙሉ ምእራፍ ተፅፎላታል። እመ ብርሃን...re



















