ሐሙስ:- ሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓ∙ም የጀነራል ዊንጌት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅን ድህረ-EASTRIP ፕሮጀክት… — General Wingate Polytechnic college-Official channel — TG.ME

ሐሙስ:- ሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓ∙ም
 
የጀነራል ዊንጌት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅን ድህረ-EASTRIP ፕሮጀክት ዘላቂነት የሚያረጋግጥ የምክክር መድረክ ተካሄደ!!
 
የEASTRIP ፕሮጀክት መጠናቀቅን ተከትሎ የጀነራል ዊንጌት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅን ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል የሚያስችል የዘላቂነት ማስተር ፕላን ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሄደ።
 
በዚህ መድረክ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ በከተማ አስተዳደሩ ስር የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ዲኖች፣ የኢንዱስትሪ ተወካዮች  ተሳትፈዋል።
 
 የምክክር መድረኩ ዋና ዓላማ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ተቋማት ከፕሮጀክት ጥገኝነት በመውጣት ራሳቸውን ችለው መቀጠል እንዲችሉና ከፕሮጀክት ድጋፍ ወደ መንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት (PPP) የሚሸጋገርበትን ስልታዊ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሆነ ተገልጿል።
 
በግምገማው ወቅት ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ኮሌጁ ራሱን ችሎ መቀጠል እንዲችል የውስጥ የገቢ አቅሙን የሚያሳድግበት ስልታዊ አቅጣጫዎች የተቀመጡ ሲሆን ሌሎች ኮሌጆችም የጀነራል ዊንጌት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅን መልካም ተሞክሮ በመውሰድ ለውጥ ለማምጣት ትልቅ መነቃቃት ሊፈጥሩ እንደሚገባ ተመላክቷል።
 
በአሁኑ ወቅት በአጋርነት ከጀነራል ዊንጌት ጋር አብሮ ለመሥራት ፍላጎት አሳይተው ወደ ሥራ የገቡ በርካታ አካላት መኖራቸውንና በቀጣይም አብረው ለመሥራት አቅደው በዝግጅት ላይ ያሉ በርካቶች መሆናቸው ተገልጿል።
 
ከጋራ ውይይቱ በተጨማሪ በተካሄዱ ተናጠል ስብሰባዎች የቢሮው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የኮሌጅ ዲኖች በግልና መንግሥት አጋርነት (PPP) አተገባበር ዙሪያ ትኩረት አድርገው የመከሩ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ የአድቫይዘሪ ቦርድ አባላት በበኩላቸው የነበራቸውን የሥራ እንቅስቃሴና አፈፃፀም ገምግመው በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አድርገዋል።
 
የመድረኩ ተሳታፊዎች ፕሮጀክቱ ለሀገሪቱ ብቁና የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ያለውን ከፍተኛ ፋይዳ በማድነቅ በቀሪው የፕሮጀክት የሥራ ጊዜ የሚከናወኑ ተግባራት በግልጽ ዕቅድና መሪ አቅጣጫ እንዲመሩ በጋራ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በተለይም በኮሌጆችና በኢንዱስትሪዎች መካከል ያለው ቅንጅትና ትስስር ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ የቀረበ ሲሆን ውይይቱ የኮሌጆችን ዘላቂ እድገት ለማረጋገጥ ትልቅ መሠረት የጣለ እንደነበር ተጠቁሟል።
 
"በላቀ አገልግሎት የመረጃ ተደራሽነት"
❤16👍2
August 6, 2026 9K 3