ቅዳሜ:- ነሐሴ 16 ቀን 2018 ዓ∙ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ይፋ ሆነ!! የዘንድሮው የ12ኛ… — General Wingate Polytechnic college-Official channel — TG.ME

ቅዳሜ:- ነሐሴ 16 ቀን 2018 ዓ∙ም

የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ይፋ ሆነ!!

የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ይፋ መደረጉን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በትምህርት ዘመኑ ፈተናውን ለመውሰድ ከተመዘገቡ 563 ሺህ 960 ተማሪዎች መካከል 550 ሺህ 210 ተማሪዎች ፈተናውን የወሰዱ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 12.8 በመቶ (70 ሺህ 544 ተማሪዎች) 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ በማምጣት ማለፍ ችለዋል።

50 ከመቶ እና ከዚያ በላይ ካመጡ ተማሪዎች መካከል በተፈጥሮ ሳይንስ 16.5 በመቶ እንዲሁም በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 8.33 በመቶ ናቸው።

የተመዘገቡ ከፍተኛ ውጤቶችን በተመለከተ ተፈጥሮ ሳይንስ በወንድ 591.6 ከ 600 እና በሴት 583 ከ 600 ሲሆን በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ በወንድ 576.2 እና በሴት 569.1 ነው።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደገለጹት የዘንድሮው ውጤት ከባለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ በመሆኑ የሚቀበሉት የሬሚዲያል ተማሪዎች ቁጥር የሚቀንስ ሲሆን የመቁረጫ ነጥቡ ወደፊት የሚገለጽ ይሆናል።

ተማሪዎች ውጤታቸውን ከሰኞ ጠዋት ወይም ማክሰኞ ከሰዓት ጀምሮ መመልከት የሚችሉ ሲሆን ቅሬታ ያላቸው ተማሪዎችም ለ5 እና 6 ቀናት ቅሬታ ማቅረብ ይችላሉም ተብሏል።

የብሔራዊ ፈተና ውጤት መለቀቁን ተከትሎ ጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅም የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በሚቆርጠው የመግቢያ ነጥብ መሠረት የ2019 ዓ.ም አዲስ ሰልጣኞችን ለመቀበል ሙሉ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቋል።

ኮሌጁ በ11 ዲፓርትመንቶች እና 30 በሚደርሱ የሙያ መስኮች በቀን፣ በማታ እና በቅዳሜና እሁድ መርሃ ግብሮች ለማሰልጠን ሰብዓዊና ቁሳዊ ግብዓቶችን በማሟላት አዲስ ሰልጣኞችን ለመቀበል ዝግጁ ነው።

"በላቀ አገልግሎት የመረጃ ተደራሽነት"
❤38👍11👎8
August 22, 2026 5.6K 27