ሰኞ:- ሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ⚽️ የኮሌጁ አሰልጣኞች የክረምት እግር ኳስ ውድድር በድምቀት ተከፈተ!… — General Wingate Polytechnic college-Official channel — TG.ME

ሰኞ:- ሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም
 
⚽️  የኮሌጁ አሰልጣኞች የክረምት እግር ኳስ ውድድር በድምቀት ተከፈተ! የአይሲቲ ዲፓርትመንት ደግሞ የጎል ናዳ አዘነበ!
 
በጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የተዘጋጀው የአሰልጣኞች የክረምት ስፖርታዊ የእግር ኳስ ውድድር በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀመረ። የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ባገኘበት ማግስት የተጀመረው ይህ የአሰልጣኞች ውድድር ስድስት የተለያዩ ዲፓርትመንቶችን የሚወክሉ ቡድኖች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
 
በዚህ ውድድር አውቶሞቲቭ ዲፓርትመንት (Turbo Striker)፣ ጀነራል መካኒክስ /GM/ ( Iron Man)፣ አይሲቲ ዲፓርትመንት (Wingate Best)፣ አግሮ ቢዝነስ (ከተማ ግብርና እና የቢዝነስ)፣ ኤሌክትሪክና ሰርቬይንግ እና ኮንስትራክሽን (ኮንስትራክሽንና ውድ ወርክ)  ባከተተ ምድብ ተከፍሎ የሚካሄድ ሲሆን የደረጃና የፍጻሜውን የዋንጫ ጨዋታ ጨምሮ በአጠቃላይ 10 የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ይስተናገዳሉ።
 
የምድብ ጨዋታው ሲጠናቀቅ ሶስተኛ የሚወጡት ቡድኖች የሚሰናበቱ ሲሆን፤ ከየምድቡ አንደኛ እና ሁለተኛ የሚወጡት አራት ቡድኖች ወደ ቀጣይ ዙር ጨዋታ ያልፋሉ። አሸናፊውን ለመለየትም የአንደኛው ምድብ አሸናፊ ከሌላኛው ምድብ ሁለተኛ ጋር ይፋለማል።
 
በዛረው የመክፈቻው ጨዋታ ላይ ሁለት ምድቦች ግጥሚ ያደረጉ ሲሆን መጀመሪያ ላይ አውቶሞቲቭ (Turbo Striker) ከ ጀነራል መካኒክስ (Iron Man) ጋር ተፋልመዋል፡፡
 
 በዚህ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች እጅግ ማራኪ የሆነ የማጥቃት እና የመከላከል ብቃት ያሳዩ ሲሆን እስከ እረፍት  ሰዓት ድረስ ባደረጉት ጠንካራ ፉክክር ጨዋታው ያለ ምንም ግብ ተጠናቆ ከእረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች አቻ የሚያደርጋቸው አንድ አንድ ግብ በማስቆጠር 1 ለ 1 በሆነ ውጤት ነጥብ ተካፍለዋል።
 
በሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ አይሲቲ ዲፓርትመንት (Wingate Best) ከ ኮንስትራክሽን ጋር የተደረገ ሲሆን አይሲቲ ዲፓርትመንት ኮንስትራክሽንን 11 ለ 5 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፍ አስገራሚ የበላይነቱን አሳይቷል።
 
 አይሲቲ ዲፓርትመንት ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በተደጋጋሚ በማምራት በርካታ ግቦችን አከታትሎ በማስቆጠር ድንቅ አጨዋወት ሲያሳይ ኮንስትራክሽን ዲፓርትመንቶች ደግሞ በአቅም የተፈተኑበትና አንድ ደርዘን የሚጠጉ ግቦችን ያስተናገዱበት ፈታኝ ጨዋታ ሆኖ አልፏል።
 
የኮሌጁ የክረምት ስፖርታዊ ውድድር በእግር ኳስ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን የሰራተኞችን የእርስ በእርስ ግንኙነት እና ጤንነት ለማጎልበት ታስቦ የመረብ ኳስ እና የጠረጴዛ ቴኒስ ጨዋታዎችም ጭምር  ይካሄዳሉ።
 
ውድድሩን በአሸናፊነት ለሚያጠናቅቁ ቡድኖች የዋንጫ ሽልማት እንደሚበረከት አዘጋጅ ኮሚቴው የገለጸ ሲሆን የዛሬው የመክፈቻ ቀን እጅግ የተሳካና የተመልካችን ቀልብ የሳበ በመሆኑ በቀጣይም ይህ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
 
 "በላቀ አገልግሎት የመረጃ ተደራሽነት"
❤20👍4🙏2✍1
July 20, 2026 8.3K 3