ወግ ብቻ: post #5380 — TG.ME

በወጣቶች የተቋቋመ Christ way የሚባል International church ቃል ልካፈል ገባሁ።

ሙሉ ለሙሉ ወጣቶች ናቸው። ሙዚቀኞቹ ፣
ሰባኪዎቹ ፣ ዲያቆናት ፣ ዘማሪዎች ሁሉም ወጣቶች ናቸው።

በየወንበሩ ተመስጠው በሚፀለዩ ሴቶች ውብት እየተዋከብኩ አንዲት የማለዳ የምንጭ ውሀ የመሰለች ልጅ ጎን ለፀሎት በተነጠፈ ጅባ ላይ ቁጢጥ ብዬ የሚካሄደውን ማስተዋል ጀመርኩ።

አንድ ስድስት ሰባት መፅሀፍ ቅዱስ የያዙ ወጣቶች በየረድፉ እየዞሩ ምእመኑ ላይ እጅ እየጫኑ ይፀያሉ።

አንዱ በልሳን እያወራ ወደኔ ቀረበ።እጁን ጭኖ ሊፀልይብኝ ነው ገብቶኛል። ባልወድም ልታገሰው ወሰንኩ። ግምቴ ልክ ነበር!

"ዛሬ በእግርህ ትሄዳለህ" ሲል ግንባሬን ይዞ ጸለየልኝ።

ምን ሆኖ ነው ብዬ ስገረም ድደገመው!
In the name Jesus Christ ዛሬ በእግርህ ትሄዳለህ"

ወደ ጆሮው ጠጋ ብዬ "አባት ምንም አልሆንኩም እኮ አሁንም መራመድ እችላለሁ" አልኩ። ሊሰማኝ አልወደደም።

ሌላኛውም ወደኔ ቀረበ

እጁን ጭኖ የልጁን ፀሎት ደገመው።
"ሳይታወቀኝ ሽባ ሆኜ ይሆን ወይስ እኚህ ሰዎች ሽባ ሆኜ ታየኋቸው" እያልኩ ግራ ተጋባሁ።

ለዚህም ለመጀመሪያው ያልኩት ደገምኩለት።አልሰማኝም።

አንዲት ቆንጆ ሴት በከፊል ዓይኗን ጨፍና ቀረበችኝ። ልጂቱ ደስ ስለምትል ደስ አለኝ።

ደስታዬን ሳልጨርስ እሷም እጇን ጭና የነሱን ፀሎት ሰለሰችኝ።

እጇን ወዲያ ልወረውረው ነበር። ግን የእጇ ልስላሴና ፊት ለፌቴ ድንቅ ያለው ስድር ጡቷ ጸሎቷን ባልወደውም እንዳስጨርሳት አስገደደኝ።

ጨረሰች! በንፅህ መንፈሳዊነት ጸጉሬን ዳብሳው "በርታ" ብላኝ ሄደች።

ስለሰለቸኝ ወጣሁ!

ስወጣ ግን ያየሁትን ነገር ማመን አልቻልኩም።
ፀሎታቸው ታወሰኝ። ዛሬ በእግርህ ትሄዳለህ!
ልክ ነበሩ ይኸው በእግሬ ሄድኩ!

ሳይክሌን ካስቀመጥኩበት አጣሁት!!

By Sintayew Addisu

@wegoch
@wegoch
@paappii
😁149❤28
July 5, 2026 6K 45