ታክሲ ውስጥ ስለገጠመኝ ሰውዬ እያዋራኋት ነው። በጣም ስላሳቀኝ መስማት እንዳልፈለገች እያወቅኩ ነው የማወራት።… — ወግ ብቻ — TG.ME

ታክሲ ውስጥ ስለገጠመኝ ሰውዬ እያዋራኋት ነው። በጣም ስላሳቀኝ መስማት እንዳልፈለገች እያወቅኩ ነው የማወራት። ለንቦጯን ብትጥልም በጨዋታው ላይ ስለተማመንኩ ወሬዬን ቀጠልኩ።
ረዳቱ «ለህፃኑም ትከፍላለህ!» ሲለው ሰውዬው «አልከፍልም» ይላል!
«ትከፍላለህ!»
«አልከፍልም!»
«ካልከፈልክ ወንበር አይዝም።»
«ይይዛል!»
«ከያዘ ክፈል!»
«አልከፍልም!!»
«ካልከፈልክ እቀፈው?!»
«ይከብደኛል!»
እኔ 😂
እሷ 😑
«በቦታው ብትኖሪ በጣም ነበር የሚያስቅሽ» አልኩ ሀፍረቴን እያፋፈስኩ።
«ብታይ ረዳቱ ራሱ ሰውዬው እንደዛ ሲል ዙሮ ሁላችንም አዬን...የታክሲው ሰው እንዳለ አፍሮ ዝም አለ...እኔ ነኝ ያቃተኝ...'ቡፍፍፍ' ብዬ መሳቅ ስጀምር ሁሉም ያፈነውን ሳቅ ለቀቀው። ታክሲዋ በሳቅ ተሞላች! ሰውዬው ስንስቅበት የተናገረው እሱም ገባው መሰለኝ እንዴት ሽምቅቅ እንዳለ!» የሆነ ሰው ዝም ብሏችሁ ምን እንደምታወሩ ግራ ገብቷችሁ ያውቃል?

«ላገባ ነው!!»

ያስገርመዋል ብላ ያሰበችውን ያህል አልተገረምኩም። ያዘዘኩትን ውሀ ጎንጨት ብዬ ወሬዬን ቀጠልኩ! መጠዬቅ ፈርቼ ነውጂ I know something was off ሰሞኑን!
«ብር አለው?»
«አዎ።»
«እድሜውስ?»
«ምራቁን የዋጠ»
ሳይታወቀኝ ምራቄን ዋጥኩ። ምራቁን የዋጠ ስንት አመት ማለት ነው?
«ስታይው ተመቸሽ?»
«መጥፎ አይመስለኝም»
የመጀመሪያ ቀን አብረን ያደርን ለታ «መጥፎ አይደለህም» ያለችኝ ትዝ አለኝ።
«ሽማግሌ ተላከ?»
«አዎ»
«ደስ ይላል!»
«እእእ»
ከአንድ አመት ፍቅረኛህ ጋር እንደዚህ ማውራት ህልም ይመስላል። ነገር ግን ሁለታችንም በውስጣችን መቼም እንደማንጋባ እናውቅ ነበር መሰለኝ አልከበደንም። ተነስታ ስትሔድ ልቤ ውስጥ የሆነ ሸርተት የሚል ሀዘን ተሰማኝ። አለ አይደል የሆነ የበረዶ ግግር ግምስ ብሎ ወደታች ሲወርድ? ልክ እንደዛ! ምን እንደሆነ አልገባኝም!

እንድንጋባ ስንቴ ለመነችኝ! እኔም ለመጀመሪያ ጊዜ «ይቺ ልጅ አንድ አራት አመት ከታገሰችኝ አገባታለሁ» የሚል ሀሳብ በልቤ ሽው እንዲል ያደረገችው እሷ ናትና እንድትቆይ ፈልጌ ነበር። አልሆነም እንጂ!

«እኔ እና አንተ ብንጋባ ነበር ትክክለኛ የአብረሀም እና የሳራ የሚሆነው»
«እኔ ከሰራተኛችን ስለምወልድ?»
«ስነስርዓት ይኑርህ እሺ! ባለጌ! እሱ እኮ ተገዶ ነው ያን ያደረገው»
«ታዲያ ምናለበት ትዳራችሁ የአብርሀም እና የሳራ ይሁን መባሉ ቢቀር?»
«ቆይ አንተ ግን ራስህን ፈልገህ ሳታገኝ ጌታውን ፈልጎ ያገኘውን አብርሀምን ልትተች ስትነሳ ትንሽ አይከብድህም?»
እንዲሁ ልክ ልኬን ስትነግረኝ ነበር ድስቴ እንደሆነች ግጣሟ እንደሆንኩ የሚገባኝ። አልሆነም እንጂ።

ገና እግሯን ሳዬው ነበር ያፈቀርኳት። እግሯ የምታምር ሴት ለትዳር የምትሆን ይመስለኛል። ለኔ ውስጣዊ ውበት ማለት የእግር ውበት ነው። እግሯ የሚያምር ሴት መርዛማ መሆን የምትችል አይመስለኝም። ቆንጆ እግር ክንፍ ነው...መለአክ ያደርጋቸዋል። እኛ ስንራመድ እነሱ ይበራሉ። ታዲያ አንድ ቀን በዚህ ክንፍ እንዳትበርብኝ እሰጋ ነበር።

«ምን እንደሚያስለቅሰኝ ታውቃለህ?» አልኩት ግሮሰሪ ያገኘሁትን ስትሬንጀር!
«ምን» አለኝ ብቻዬን ተወኝ በሚመስል ቅላፄ
«እሷን ማጣቴ ምንም አልመሰለኝም። የሚያስለቅሰኝ የኔ እንዲህ ሁኖ መቅረት ነው። አይኔ እያዬ ሶስት ሴቶቼ ጥለውኝ ወደ ትዳር ገቡ። ሶስት!» ያወጣኋቸው ጣቶች ሶስት መሆናቸውን ለማረጋገጥ ደግሜ አየሁት። ሁለት ናቸው። አንዱን ጨመርኩት።
«እ» አለኝ! «እ» አባባሉ እሽ ቀጥል ሳይሆን 'እ' ን የተደገፋት ነው የሚመስለው እእእእ አይነት! ገብቶኛል በቃ ተወኝ መሰለኝ የሚለው። ተናደድኩና ዝምብዬ መጠጣት ጀመርኩ። ዝም ስል እንዳኮረፍኩ ገባው መሰለኝ በጥፋተኝነት ስሜት ሊያዋራኝ ሞከረ።
«ታፈቅራታለህ?»
«እእእእ»
«ይሔን ያህል ከፈለካት ለምን አታገባትም?»
«አላገባም»
«ግዴለህም አግባት!»
«አላገባም!»
«ስለዚህ ሌላ እንድታገባ ትፈልጋለህ ማለት ነው?»
«አልፈልግም።»
«እንደዛ ካልሆነ አግባታ?!»
«አልችልም።»
የጧቱ ሰውዬ አባባል አሁን ገና ነው የገባኝ። ክፈል...አልከፍልም...ካልከፈልክ እቀፈው...ይከብደኛል። ለካስ ከውጭ ሲታይ የሚያዝናናው ሁሉ ከውስጥ ህመም ነው። ሌላ ታግባ...አልፈልግም...እንደዛ ከሆነ አግባታ....አልችልም። አብሮኝ የሚጣጠው በውዝግቤ ተገርሞ ይስቅብኛል። የሚሰማኝ ግን ያንን አባት ስስቅበት የነበረው የራሴ ድምፅ ነው። ከህይወት ክብ ወዴት ይመለጣል?

By Mickel Azmeraw

@wegoch
@wegoch
@paappii
❤76👏35
July 2, 2026 5.6K 29