የፓኪስታን የጦር አዛዥ ቴህራን ገብተዋል ተባለ
የፓኪስታን የጦር አዛዥ በዋሽንግተንና በቴህራን መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ ቴህራን ገብተዋል፡፡
የፓኪስታን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ እና የደህንነት ኃይሎች መሪ ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር፤ከከፍተኛ የኢራን ባለስልጣናት ጋር ለመወያየት ወደ ቴህራን እንዳቀኑ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ይህ ጉብኝት ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር በዩናይትድ ስቴትስ፣ በእስራኤል እና በኢራን መካከል ያለውን ጦርነት ለማስቆም እና ሰላም ለማውረድ የሚያደርጉትን ጥረት ለመቀጠል ዘንድሮ ወደ ኢራን ያደረጉት ሶስተኛው ጉብኝት ነው ተብሏል።
ፓኪስታን በቴህራን እና በዋሽንግተን መካከል የግንኙነት መስመር መሆን እንደምትችል ብትገልጽም፤ተንታኞች ግን ሀገሪቱ ያላትን ትክክለኛ ተፅዕኖ በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶችን እየሰጡ ይገኛሉ።
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባጋኢ ጉብኝቱ በምዕራብ እስያ ቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋትን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ጉብኝት የተደረገው ቀደም ሲል በኢስላማባድ የተጀመረው የሰላም ስምምነት ጥረት በቆመበት እና ዋሽንግተን አዲስ ማዕቀብ በማዘጋጀት ላይ ባለችበት ወቅት ነው ሲል አልጀዚራ ዘግቧል።