Orthodoxy: post #850 — TG.ME

ክርስቶስ

ስንኖርም ለዘለዓለም እንዳንጠማ የሚያደርግ ለዓለም የተሰጠ የህይወት መጠጥ እርሱ ነው። እንዳንራብ እራሱን ለዓለም የሰጠ የዘለዓለም የሕይወት ምግብ እርሱ ነው።

በጎ ብናደርግ የምንወርሰው መንግስታችን እርሱ ነው። ለዘለዓለም የምንጠጋበት የነፍሳችን እረፍት እርሱ ክርስቶስ ነው። ለእኛ ሲል ከሰማያት ሲወርድ ከመላእክት ዝቅ ሲል አለቅነቱን እንደመቀማት አልቆጠረውም። በደሙ ፈሳሽነት የጎሰቆለ ተፈጥሮችን ወደ ቀደመ ክብሩ የመለሰ እርሱ ነው።

የአዳምን አምላክ የመሆን መሻት የፈጸመ እርሱ ነው። ይኼንም በገሊላ አውራጃ በምትኖር በአንዲት ድንግል ማህፀን በአደረ ጊዜ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ ሲዋሐድ /ሥጋዌ —incarnation / የሔዋን መሻት ተፈጸመ ።

የነብያቱን ትንቢት የፈጸመ ፤ የአበውን ተስፋ ፤ የቅዱሳኑን ጸለቶ የተቀበለ እርሱ ክርስቶስ ነው። የሆነው ሁሉ በእርሱ የሆነ ፤ በጥቂቱ እንደ ሰው ያደገ ፤ ከላይ ከሰማይ ያልጎደለ ከታችም ያልተጨመረበት ፤ ከሐዋርያቱ ጋር በታንኳ ሲጓዝ ያንቀላፋ ፤ ማዕበሉን ፀጥ እንዲል ያደረገም እርሱ ነው።

ከማርያም የተወለደ እርሱ በቀደመ ልደቱ ከአብ የተወለደውም እርሱ ነው። የመጀመሪያ እና የመጨረሻም እርሱ ነው። ከማርያም በመወለዱም ዘመን የተቆረጠለት እርሱ ነው።

የነፍሳችን እረፈት እንወደው ዘንድ ስለ እኛ ደም ግባት የሌለው መድኃኒታችን እርሱ ክርስቶስ ነው። ወንጌላችንም ስብከታችን እርሱ ነው።

#ማስያስ
#orthodoxy
🥰3🙏1
July 30, 2026 222 1