የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) ዕዞች የ2019 ዓ/ም የትምህርት ዘመን መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ በይፋ እንዲጀመር ጥሪ አቅርበዋል!
ትምህርት ለአንድ ሀገር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እድገት ወሳኝ መሠረት መሆኑ በውል የሚታወቅ ሲሆን፤ ሀገራችን ከገጠማት ውስብስብ ችግር እና የጸጥታ ስጋት አንጻርም ጭምር የትምህርትን አስፈላጊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የ2019 ዓ/ም የትምህርት ዘመን በወቅቱ እና በአግባቡ እንዲጀመር የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) ዕዞች ጥሪ አስተላልፈዋል።
የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) ባስቀመጠው አጠቃላይ አቅጣጫ መሠረት፦
፩. አፋብን ሸዋ ጠቅላይ ግዛት አሳምነው 5ኛ ዕዝ (በማኅበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አርበኛ አስታወሰኝ ላቀ በኩል) እንደገለጸው፤ ትምህርት ሰላም እና መረጋጋት ቢፈልግም፣ ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ አኳያ በስጋት ውስጥ ሆነንም ቢሆን የ2019 ዓ/ም የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ በወቅቱ እንዲጀመር አቅጣጫ ተቀምጧል። በመሆኑም በየደረጃው ያሉ የፋኖ አመራሮች፣ ወላጆች፣ መምህራን፣ ርዕሰ መምህራን እና የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።
፪. አፋብን ጎጃም ጠቅላይ ግዛት ቴዎድሮስ 2ኛ ዕዝ ለሁሉም ኮሮች ባስተላለፈው ጥሪ፣ ድርጅታችን ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት መደበኛ ትምህርት እንዲጀመር አሳስቧል። ለዚህም ስኬት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እንዲደረግ አሳስቦ፣ ሁሉም ኮሮች ትምህርት እንዲጀምሩ ጥሪ አቅርበዋል።
፫. አፋብን ጎንደር ጠቅላይ ግዛት በላይ ዘለቀ 3ኛ ዕዝ (በማኅበራዊ ጉዳይ መመሪያ ኃላፊ አርበኛ ብዙአየሁ ወንድምነው አማካኝነት) በሰጠው መግለጫ፣ ድርጅቱ ያስቀመጠውን አቅጣጫ መሠረት በማድረግ በዕዙ ሥር የሚገኙ ሁሉም ኮሮች አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርገው ትምህርት እንዲያስጀምሩ አሳስቧል። ሙሉው ሕዝብ፣ መምህራን፣ የተማሪ ወላጆች እና ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ ተላልፏል።
፬. አፋብን ወሎ ቤተ-አማራ ጠቅላይ ግዛት ምኒልክ 1ኛ ዕዝ በሰጠው ማሳሰቢያ፣ የ2019 ዓ/ም የትምህርት መርሐ ግብር እውን እንዲሆን በቁጥጥራቸው ሥር በሚገኙ አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ወደ ሥራ እንዲገቡና የምዝገባ ሥራዎች እንዲጀመሩ አሳስቧል፤ ለዚህም አስፈላጊው ትብብር እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።
በአጠቃላይ የአፋብን ዕዞች ባስተላለፏቸው መልእክቶች፤ ትውልድን ለማዳን፣ አስተሳሰብን ለመገንባት እና ትናንትን በአዲስ ተስፋ ለመተካት ትምህርት ቤቶች መደበኛ አገልግሎታቸውን እንዲጀምሩና መላው የህብረተሰብ ክፍል አስፈላጊውን እገዛና ትብብር እንዲያደርግ አጽንኦት ተሰጥቷል።
ምንጭ፦የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ(አፋብን) ወታደራዊ ቃል አቀባይ
5September 3, 2026 1.5K