ቃጭሉን የሚያስረው ማነው?
ድመቷ አይጦችን እያደነች ቁም ስቅላቸውን ስታሳይ፣ አይጦች ተሰብስበው ይህንን ችግር ለመቅረፍ መከሩ። አንዷ አይጥም "ድመቷ ስትመጣ እንድንሰማ አንገቷ ላይ ቃጭል እንሰርላት!" የሚል ምርጥ ሃሳብ አቀረበች። ሁሉም አይጦች በደስታ ጨፈሩ፤ ሃሳቡንም ደገፉት።
ነገር ግን... በመጨረሻ አንዲት አሮጊት አይጥ ተነስታ "ሃሳቡ ግሩም ነው፤ ሆኖም ቃጭሉን ሄዶ ድመቷ አንገት ላይ ማን ያስራል?" ስትል ስብሰባው በዝምታ ተዋጠ።
ትልቅና የሚያምር እቅድ ማውጣት ብቻውን በቂ አይደለም፤ ዋናው ቁምነገር እቅዱን ወደ ተግባር መለወጥ ነው። ብዙ ጊዜ ለውጥ የሚመጣው ዝም ብሎ በማውራት ሳይሆን፣ አስፈሪውንና ከባዱን የመጀመሪያ እርምጃ ደፍሮ የሚጀምር ሰው ማግኘት ነው።
....
በየማህበራችን፣ በየስራ ቦታችን አልፎ ተርፎም በሃገራችን... ሃሳብ የሚያቀርብ ሞልቷል። ግን ቃጭሉን የሚያስረው ማን ነው?
ማዕደ ጥበብ -
ምንጭ፡ አዲስ አድማስ



