በኦቲዝም ውስጥ የሚታይ የክህሎት መቀነስን (Regression) መረዳት
የክህሎት መቀነስ (Regression) ምንድን ነው?
Regression ወደ አማርኛችን ስንመልሰው ማሽቆልቆል/መመለስ/ወደኋላ መመለስ ማለት ሲሆን ይህም አንድ ልጅ ቀድሞ የተማራቸውንና ያዳበራቸውን ክህሎቶች መልሶ ሲያጣ ማለት ነው።
ይህም የሚከተሉትን ሊያካትት ይችላል፦
- የንግግር መቀነስ ወይም ቃላትን መርሳት
- የአይን ንክኪ ወይም ማህበራዊ ግንኙነት መቀነስ
- የጨዋታ ወይም የዕለት ተዕለት ክህሎቶችን (እንደ ራስን መመገብ፣ መልበስ) ማጣት
- የባህሪ መለዋወጥ (ቶሎ መቆጣት) ወይም ራስን ማግለል
* ይህ ሁኔታ በድንገት ወይም በሂደት ሊከሰት ይችላል።
የክህሎት መቀነስ (Regression) ለምን ይከሰታል?
ለዚህ አንድ ወጥ የሆነ ምክንያት ባይኖርም፣ የተለመዱት መንስኤዎች የሚከተሉት ናቸው፦
- የአንጎል እድገት ለውጦች፦ የልጆች እድገት ፍጥነት የተለያየ ነው። አንዳንድ ጊዜ አንጎላቸው ራሱን መልሶ በሚያደራጅበት ወቅት በክህሎቶቻቸው ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።
- ውጥረት ወይም ትልልቅ ለውጦች፦ አዳዲስ ነገሮች ለልጁ ከአቅም በላይ ሊሆኑባቸው ይችላሉ። ለምሳሌ፦ አዲስ ትምህርት ቤት፣ የመኖሪያ ቤት መቀየር፣ አዲስ ጨቅላ ህጻን ወደ ቤት ሲመጣ ወይም የለመዱት የዕለት ተዕለት ተግባር ሲቀየር።
- የመግባባት ችግር መፈጠር፦ አንድ ልጅ ፍላጎቱን መግለጽ ካልቻለ፣ ንግግርን መሞከር ሊያቆም ወይም በምትኩ በለቅሶና በንዴት ስሜቱን ሊገልጽ ይችላል።
- የጤና ወይም የስሜት ህዋሳት ችግር፦ እንደ ህመም፣ የእንቅልፍ እጦት ወይም ለከፍተኛ ድምጽና ብርሃን መጋለጥ ለክህሎት መቀነስ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ።
- ልምምድ ማነስ፦ አንድ ክህሎት በየቀኑ ካልተተገበረ ሊረሳ ይችላል።
ወላጆች እንዴት ሊረዱ ይችላሉ?
- በመረጋጋት ሁኔታውን መከታተል፦ የትኞቹ ክህሎቶች ተቀየሩ? መቼ ጀመረ? በወቅቱ ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ? የሚሉትን በማስተዋል መንስኤውን ማወቅ ይቻላል።
- ከመሰረታዊ ነገሮች መጀመር፦ ልጁ ያጣቸውን ክህሎቶች በድጋሚ በቀላል ደረጃ እናስተምረው። "ከዜሮ እየጀመርን ሳይሆን፣ የነበረውን መልሰን እየገነባን ነው" ብለን እናስብ።
- የተለመዱ ተግባራትን አለማዛባት፦ በየቀኑ ተመሳሳይ የጊዜ ሰሌዳ ይኑረን። ለውጦች ከመደረጋቸው በፊት አስቀድመን ማሳወቅ፤ ምስሎችን በመጠቀምም ነገሮችን ማስረዳት አለብን።
- የመግባቢያ መንገዶችን ማበረታታት፦ ልጁ በእጅ ምልክትም ይሁን በምስል ለመግባባት የሚያደርገውን ሙከራ ሁሉ መቀበል አለብን። ምርጫዎችን እንስጠው (ለምሳሌ፦ "ውሃ ወይስ ወተት?")።
- ጥረቱን ማድነቅ፦ ውጤቱን ብቻ ሳይሆን ሙከራውንም እናበረታታ። ለትናንሽ ስኬቶች ሽልማት እንስጥ።
- ውጥረትን መቀነስ፦ ጸጥ ያሉ ቦታዎችን እናዘጋጅለት። ለልጁ የሚረብሹትን ድምጾች ወይም ብርሃናት እናስወግድ።
- ከባለሙያዎች ጋር መሥራት፦ ከህክምና ባለሙያዎችና ከመምህራን ጋር በቅንጅት መስራት ፈጣን መሻሻል ለማምጣት ይረዳል።
ተጨማሪ እርዳታስ መቼ ያስፈልጋል?
የሚከተሉት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ባለሙያ እናማክር፦
- የክህሎት መቀነሱ እየቀጠለ ከሄደ
- ልጁ ሙሉ በሙሉ መግባባት ካቆመ
- ድንገተኛና ከፍተኛ የባህሪ ለውጦች ከታዩ
ለወላጆች ማሳሰቢያ
- የክህሎት መቀነስ የሚያስደነግጥ ቢሆንም ተስፋ አስቆራጭ ግን አይደለም።
- ብዙ ልጆች ተገቢው ድጋፍ ከተደረገላቸው ክህሎቶቻቸውን መልሰው ያገኛሉ።
- ለዚህ ሁኔታ መከሰት ተጠያቂዎቹ እኛ አይደለንም።
- የእኛ ትዕግሥትና ድጋፍ ለልጁ ትልቅ ለውጥ ያመጣል።











