#አዲስ_ዓመት
#New_Year
መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት እናንብብ? ጠቃሚ መርሆች
ክፍል-2
መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ዘላለማዊ አስፈላጊነት አለው፤ የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ልንሰማውና ልንታዘዘው ይገባናል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ቃሉን በታሪክ ውስጥ በሰው ቋንቋ ለመናገር ስለመረጠ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለ መጽሐፍ ሁሉ ታሪካዊ ውስንነት አለው፡፡ እያንዳንዱ ክፍል መጀመርያ በተጻፈበት ቋንቋ፣ ዘመንና ባሕል የተወሰነ ነው (በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ በተጨማሪም በጽሑፍ ከመስፈሩ በፊት በነበረው የአፈታሪክ ትውፊት [የተወሰነ ነው])፡፡ በዘላለማዊ አስፈላጊነቱና በታሪካዊ ውስንነቱ መካከል ያለው “ውጥረት” መተርጎምን አስፈላጊ ያደርገዋል፡፡ (Gordon D. Fee & Douglas Stuart: How to Read the Bible For All Its Worth, Second Edition, Zondervan, Grand Rapids, 1993, Introduction)
ይህ ርዕስ በጣም ሰፊና ጥልቅ ቢሆንም ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስን በግላቸው ለማጥናትና በትክክል ለመረዳት ለሚሹ ወገኖች ጠቃሚ የሆኑ ምክረ ሐሳቦችን ብቻ አጠር አድርገን እናስቀምጣለን፡፡
በሥነ ፍታቴ ውስጥ ሦስቱ መሠረታውያን ነጥቦች፡- ሐቲት፣ መተርጎምና ማዛመድ ናቸው፡፡
ሐቲት (Exegesis)
“ኤክሰጂሰስ” የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል ከግሪክ የተገኘ ነው፤ ትርጉሙም “ማውጣት” እንደማለት ሲሆን አንድ ቃል ለመጀመርዎቹ ተቀባዮች በራሳቸው ቋንቋና ባሕል ምን ማለት እንደነበር ለማግኘት የሚደረግ ሥርዓትን የጠበቀ ጥናት ነው፡፡ በሐቲት ውስጥ ሁለት መሠረታውያን ነጥቦች አሉ፡፡ የመጀመርያው አውድ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ይዘት ነው፡፡
1. አውድ
ሁለት ዓይነት አውዶች አሉ፡-
ሀ. ታሪካዊ አውድ
ይህ መጽሐፉ የተጻፈበትን ጊዜና ባሕል የሚመለከት ሲሆን የጸሐፊውንና የተደራሲያኑን መንፈሳዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥና ሌሎች ከጽሑፉ ይዘትና ትርጉም ጋር ሊገናኙ የሚችሉ ነጥቦችን ሁሉ ከግምት ውስጥ የማስገባት ሥራ ነው፡፡ የሚከተሉትን ጥያቄዎች በመጠየቅ የአንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ታሪካዊ አውድ ማወቅ እንችላለን፡-
👉ጸሐፊው ማነው? (የጸሐፊውን ስም እርግጠኛ በመሆን ማወቅ ቢሳነን እንኳ ከአጻጻፉ በመነሳት ስለ እርሱ መገመት እንችላለን)
👉ተደራሲያኑ እነ ማን ናቸው?
👉መቼ ተጻፈ?
👉የት ተጻፈ?
👉የተጻፈበት ምክንያት ምን ነበር?
ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች ጥያቄዎችን ብንጠይቅ የመጽሐፉን ታሪካዊ አውድ በቀላሉ ማወቅ እንችላለን፡፡ እነዚህን ለመሳሰሉ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት ያን ያህል የሚቸግር ባይሆንም ነገር ግን ስለ ጉዳዩ የበለጠ እውቀት ባላቸው ሰዎች የተጻፉ ጥሩ ሐተታዎችንና መዝገበ ቃላትን ብንጠቀም ግንዛቤያችን ይበልጥ ሊሰፋ ይችላል፡፡
ለ.የምንባብ አውድ
ይህ ቀላል የሆነ፣ ነገር ግን ብዙ ሰዎች ትኩረት ስለማይሰጡት በመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም ላይ ትልልቅ ስህተቶችን እንዲሰሩ ምክንያት የሚሆናቸው ነጥብ ነው፡፡ የሥነ ፍታቴ ምሑራን የዚህን መርህ አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተው ሲናገሩ “#ምንባቡ_ንጉሥ_ነው” ይላሉ፡፡ አንድን ቃል፣ ሐረግ ወይንም ደግሞ ዓረፍተ ነገር በምንባብ አውድ ውስጥ መረዳት ማለት ዙሪያ ገባውን በማንበብ በተጻፈበት በዚያ ክፍል መሠረት የሚሰጠውን ትርጉም መረዳት ማለት ነው፡፡ ዛሬ ብዙ ሰዎች፣ በተለይም ደግሞ ሙስሊም ጸሐፍት ይህንን ቀላል መርህ ባይዘነጉ ኖሮ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ “ስህተቶችና” “ግጭቶች” ብዙ በመጻፍ ባልደከሙ ነበር፡፡ በተደጋጋሚ የሚነሳውን አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል፤ የምንባብ አውዱን ባንጠብቅ መጽሐፍ ቅዱስን “አምላክ የለም” ልናስብለው እንኳ እንችላለን፡፡ መዝሙር 14፥1 “አምላክ የለም” ይላል፡፡ ነገር ግን ሙሉ ጥቅሱ፡- “ሰነፍ በልቡ አምላክ የለም ይላል። በሥራቸው ረከሱ፥ ጐሰቈሉ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም” የሚል ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በተለያዩ መጻሕፍት ታትመው የሚወጡ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ “ግጭቶችና” “ስህተቶች” የሚነገሩ አብዘኞቹ ውንጀላዎች ከዚህ የዘለለ ጥልቀት የሌላቸው ናቸው፡፡
ይቀጥላል...
ምንጭ:- www.ewnetlehulu.org
ወደ ቻናሉ ለመ🀄️ላ🀄️ል፦ @Holy_scriptures