#አዲስ_ዓመት
#New_Year
መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት እናንብብ? ጠቃሚ መርሆች
ክፍል-1
መጽሐፍ ቅዱስ ማዕከላዊ መልዕክቱ ለማንኛውም ሰው ግልፅ ሊሆን በሚችልበት ሁኔታ የተቀመጠ ስለሆነ በሁሉም የዕድሜ ክልሎችና በየትኛውም የትምህርት ደረጃ ላይ ላሉ ሰዎች መናገር የሚችል መጽሐፍ ነው፡፡ 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡14-15 ላይ ህጻናት እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስን ዋና መልዕክት መረዳት እንደሚችሉ ይናገራል፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እኩል በሆነ ሁኔታ ግልፅ ናቸው ወይንም ደግሞ በቀላሉ ለመረዳት የሚያዳግቱ ክፍሎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ማንኛውም ሰው የዘላለምን ሕይወት ማግኘት እንዲችል ማዕከላዊ መልእክቱ ብዙ ጊዜ በመደጋገምና እጅግ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ተቀምጧል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው እንድናነበው እንጂ እንደ ምትሃታዊ መጽሐፍ በመቁጠር ተንተርሰነው እንድንተኛ ወይንም ደግሞ ሊነካካ በማይችልበት ስፍራ በጥንቃቄ እንድናስቀምጠው አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በሕይወታችን ውስጥ ሊሠራ የሚችለው ሲነበብ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እንደ አድካሚ ኃይማኖታዊ ሕግጋት ስብስብ ሊታሰብ አይገባም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የሕይወት ቃል ነው፤ ሕያውና የሚሠራም ነው፡፡ ስናነበው እምነትን በውስጣችን ይፈጥራል፣ ነፍሳችንን ያድሳል፤ ይለውጠናልም፡፡ በውስጡ የተቀመጡትን ሕግጋት በራሳችን ኃይልና ጥረት ልንፈፅማቸው እንደምንችል መቁጠር አይኖርብንም፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ሐሳብ ለመኖር መጀመርያ ቃሉ በውስጣችን በሚፈጥረው እምነት በክርስቶስ ኢየሱስ አዳኝነት በማመን አዲስ ፍጥረት መሆን ያስፈልገናል፤ ከዚያም ኃይል የሚሰጠውን የክርስቶስን መንፈስ መቀበል ያስፈልገናል፡፡
የእግዚአብሔርን ቃል አንብበን የምንረዳው ሰዎች ባወጡት ቀመር መሠረት ባይሆንም ነገር ግን ሊታወቁ የሚገባቸው መርሆች አሉ፡፡ በማስከተል እነዚህን መርሆች እንዳስሳለን፡፡
የልብ ዝግጅት
አንዳድ ሰዎች በተደጋጋሚ የሚናገሩት የተለመደ ነገር ቢኖር መጽሐፍ ቅዱስን በማንበባቸው ሳብያ ትክክል አለመሆኑን እንደተገነዘቡና በቀደመው ሃይማኖታቸው እንዲፀኑ እንደረዳቸው ነው፡፡ እነዚህ ወገኖቻችን ያልተገነዘቡት አንድ እውነት ቢኖር የእግዚአብሔር ቃል ተልዕኮ ሁለት ገጽታ ያለው መሆኑን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እውነትን ለሚጠሙ ሰዎች የሕይወት ቃል ሲሆን በእውነት ላይ ለሚያምጹ ሰዎች ደግሞ የፍርድ ቃል ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ሰዎችን ወደ እምነት ያመጣል አለዚያም ደግሞ ልባቸውን በማደንደን ይገፈትራቸዋል፡፡ ሁለቱም ውጤቶች ግን ከሰዎቹ የልብ ዝግጅት አንጻር የሚከወኑ ናቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ሕይወት አልባ ንግግር ሳይሆን የሚሠራ ነው፡-
“የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል”
(ዕብ. 4፡12)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው በመጨረሻው ቀን በኛ ላይ የሚፈርደው ቃሉ ነው፡-
“ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁምና ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀው ቢኖር የምፈርድበት እኔ አይደለሁም። የሚጥለኝ ቃሌንም የማይቀበለው እርሱ የሚፈርድበት አለው፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል።”
(ዮሐ. 12፡47-48)
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮንቶስ መልዕክቱ ላይ የሚከተለውን ይናገራል፡-
“በሚድኑቱና በሚጠፉቱ ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነንና፤ ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ ለእነዚያም ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን። ለዚህም ነገር የሚበቃ ማን ነው?” 2ኛ ቆሮንቶስ 2፡15-16
ሐዋርያው እያለ ያለው ነገር ቢኖር ወንጌል ዝም ብለን የምንቀበለው ወይንም ደግሞ የምንጥለው ነገር ሳይሆን ብንቀበለው ወይንም ደግሞ ባንቀበለው በሕይወታችን ላይ ተፅዕኖ ማምጣቱ ግድ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ሲንቁ፣ መዘባበቻ ሲያደርጉና ሲያምጹበት የተሸነፉት እነርሱ እንጂ ቃሉ አይደለም፡፡ በዚህም ሆነ በዚያ የእግዚአብሔር ቃል አሸናፊ ነው፡፡ ለተቀበሉት የዘላለምን ሕይወት ሲሰጥ ባልተቀበሉት ላይ ግን ይፈርዳል፡፡ የወንጌል መልዕክት እውነትን ለማወቅ ለሚፈልጉ ሰዎች የሕይወት ዜና ነው፤ ለዘባቾች ግን የሞት ዜና ነው፡፡ ውድ አንባቢያን እናንተ የእግዚአብሔርን ቃል እውነትን በሚፈልግ ልብ ከሚያነቡት ወገን ናችሁ ወይንስ ከቃሉ ውስጥ “ስህተቶችን” ነቅሰው ለማውጣት ከሚያነቡት ሰዎች ወገን ናችሁ? ቀና በሆነ ልብ ቃሉን በማንበብ የዘላለምን ሕይወት ታገኙ ዘንድ ምኞታችንና ጸሎታችን ነው፡፡
ሥነ ፍታቴ (Hermeneutics)
የሥነ ፍታቴ ጥቅም መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን ለመጀመርያዎቹ ተቀባዮች የነበረውን ትርጉምና ዛሬም ደግሞ ለኛ ምን ማለት እንደሆነ እንድንረዳ ማገዝ ነው፡፡ በዘመናት መካከል ሰዎች ይህንን ቃል ብዙ ክፉ ሥራዎቻቸውን ለማጽደቅ ጠቅሰውታል፡፡ በዚህ ዘመንም ብዙ ሰዎች በመልካምም ሆነ በእኩይ ፍላጎት በመነሳሳት መጽሐፍ ቅዱስ ያላለውን ነገር ሲያስብሉት እናያለን፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ብዙ ሰባኪያን ትግላቸው በአንድ ጥቅስ ውስጥ ያለን ልዩ ትርጉም ማግኘት ይመስላል፡፡ የስህተት አስተማሪዎችና ከክርስትና ውጪ ያሉ የአንዳንድ ሃይማኖቶች ተከታዮችም ደግሞ የራሳቸውን አስተምህሮ ለመደገፍ ወይንም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት እንዳለበት ለማሳየት በማለም ጥቅሶችን ይጠመዝዛሉ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስን በምናጠናበት ሰዓት ከመሠረታዊ የሥነ ፍታቴ መርሆች ጋራ የሚጣረስ አተረጓጎም የምንጠቀም ከሆነ ወደ ስህተት እንገባለን፡፡ ስለዚህ ማንኛውም መጽሐፍ ቅዱስን ለግል ሕይወቱም ሆነ ሌሎችን ለማስተማር ማጥናት የሚፈልግ ሰው እነዚህን ጠቃሚ መርሆች ማወቅ ይኖርበታል፡፡
ጎርደን ዲ. ፊ. እና ዳግላስ ስቱዋርት የተባሉ ክርስቲያን ጸሐፍት የሥነ ፍታቴን አስፈላጊነት በተመለከተ የሚከተለውን ብለዋል፡-
ሥነ ፍታቴ አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳይ መርህ በመጽሐፍ ቅዱስ ባሕርይ ውስጥ ይገኛል፡፡ ቤተክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስን ባሕርይ የክርስቶስን ባሕርይ በምትረዳበት ሁኔታ ስትረዳ እንደኖረች ታሪክ ያሳያል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ጊዜ ሰብዓዊም መለኮታዊም ነው፡፡ ፕሮፌሰር ጆርጅ ላድ አንድ ጊዜ እንደተናገሩት፦ “መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ቃላት በታሪክ ውስጥ የተሰጠ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡” እንግዲህ ይህ ሁለትዮሽያዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ባሕርይ ነው እንድንተረጉመው የሚያስገድደን፡፡
ይቀጥላል...
ምንጭ:- www.ewnetlehulu.org
ወደ ቻናሉ ለመ🀄️ላ🀄️ል፦ @Holy_scriptures
11
1August 18, 2026 1.2K 1 12