ቅዱሳት መጻሕፍት: post #6683 — TG.ME

ቅዱሳት መጻሕፍት#አዲስ_ዓመት #New_Year መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት እናንብብ? ጠቃሚ መርሆች ክፍል-2 መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ዘላለማዊ አስፈላጊነት አለው፤ የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ልንሰማውና ልንታዘዘው ይገባናል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ቃሉን በታሪክ ውስጥ በሰው ቋንቋ ለመናገር ስለመረጠ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለ መጽሐፍ ሁሉ ታሪካዊ ውስንነት አለው፡፡…
#አዲስ_ዓመት
#New_Year


መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት እናንብብ? ጠቃሚ መርሆች


            ክፍል-3


የአንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የምንባብ አውድ ለመረዳት የሚከተሉትን ጥያቄዎች ልናነሳ እንችላለን፡-

👉ተናጋሪው ማነው?

👉ለማነው የተናገረው?

👉ጸሐፊው ለምን ይህንን በዚህ ስፍራ አስገባው?

👉ከፊት ምን ተባለ?

👉ከኋላ ምን ተባለ?

👉ይህ ቃል፣ ሐረግ ወይም አረፍተ ነገር በዚህ ስፍራ ላይ የሚሰጠው ትርጉም ምንድነው?

👉ዋናው ጭብጥ ምንድነው?

ማንኛውንም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በተጻፈበት አውድ ውስጥ ለመረዳት እነዚህንና መሰል ቀላል ጥያቄዎች ማንሳት ጠቃሚ ነው፡፡

2. ይዘቱን ማተት

ይዘት ከቃላትና ሐረጎች ትርጉም፣ የሰዋሰው አወቃቀርና በጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች ውስጥ የተለያዩ አነባበቦች የሚገኙ ከሆነ ትክክለኛውን ከመምረጥ ጋር ይያያዛል፡፡ እነዚህን ነጥቦች ለማወቅ በዘርፉ ላይ ዕውቀት ባላቸው ሰዎች የተጻፉ የተለያዩ ሐተታዎችንና መዝገበ ቃላትን መጠቀም በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እኛ ከለመድናቸው ትርጉሞች የተለየ ትርጉም ያላቸው ቃላትና ሐረጎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እንደምሳሌ ለማንሳት ያህል የጥንት አይሁዳውያን ማንኛውንም የቀን ክፍል እንደ ሙሉ ቀንና ሌሊት ነው የሚቆጥሩት፡፡ ለምሳሌ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ማለት የግድ 72 ሰዓታት ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የአማርኛ ቃላት እንኳ ሆነው በትክክል የማንረዳቸው ቃላትና ሐረጎች ያጋጥማሉ፡፡ 

መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን የነበሩ የተለያዩ መለኪያዎች፣ የቀን አቆጣጠሮችና የመሳሰሉት እኛ ከምናውቃቸው የተለዩ ስለሆኑ ምን ማለት እንደሆኑ ለማወቅ መዝገበ ቃላትን ወይንም ደግሞ ሐተታዎችን መጠቀም ያስፈልገናል፡፡ ሌላው ስለ ይዘት ሲታሰብ ሊታወቅ የሚገባው ነገር ቢኖር አንዳንድ ጊዜ የዓረፍተ ነገሮች ሰዋሰዋዊ አወቃቀር ዓረፍተ ነገሩ የተለያዩ ሁለት ትርጉሞች እንዲኖሩት ሊያደርግ መቻሉ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ሌሎች ትርጉሞችን ማየት ወይንም ደግሞ ሐተታዎችን በመጠቀም በመጀመርያዎቹ ቋንቋዎች ውስጥ ያለውን ትርጉም መፈለግ ጠቃሚ ነው፡፡

መተርጎም

ይህ ርዕስ እጅግ ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ወደ ውስጥ ጠልቀን በመግባት እያንዳንዱን ነጥብ መተንተን ስለማንችል ጠቅለል ባለ ሁኔታ መሠረታዊውን ሐሳብ ብቻ እናስቀምጣለን፡፡ በመጀመርያው ምዕራፍ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ዓይነት የሥነ ጽሑፍ ዘይቤን ያልተከተለ መሆኑን ገልፀናል፡፡ ለተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ዓይነቶች የተለያዩ አተረጓገሞችን እንጠቀማለን፡፡

#የሕግ_መጻሕፍት- የብሉይ ኪዳን ሕግጋት በ 3 ይከፈላሉ፡፡ እነርሱም:-

ሀ. የግብረገብ ሕግጋት

ለ. የሥርዓት ሕግጋትና

ሐ. የማሕበረሰብ ሕግጋት ናቸው፡፡

የግብረገብ ሕግጋት የማይለወጠውን የእግዚአብሔርን ባሕርይ የሚገልጹ ስለሆኑ ሊለወጡ ወይንም ደግሞ ሊሻሻሉ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሕግጋት በየትኛውም ዘመን ሊጠበቁ ይገባል፡፡ ለምሳሌ አትግደል፣ አትስረቅ፣ አታመንዝር ወዘተ. የሚሉት እነዚህ ሕግጋት የግብረገብ ሕግጋት ስለሆኑ ዓለም አቀፋዊ ናቸው፡፡ የሥርዓት ሕግጋትና የማሕበረሰብ ሕግጋት ግን ለእስራኤላውያን ብቻ የተሰጡ ናቸው፡፡ የሥርዓት ሕግጋት ስለ መቅደሱ የአምልኮ ሥርዓቶች፣ ስለሚበሉና የማይበሉ እንስሳት፣ ስለ መንጻት ሥርአቶች፣ ወዘተ... የሚናገሩ ናቸው፡፡ አይሁዳውያን ያልሆኑ ሕዝቦች እነዚህን ሕግጋት የመጠበቅ ግዴታ የለባቸውም፡፡ የማሕበረሰብ ሕግጋት ደግሞ የጋብቻ ሥርዓቶች፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግጋት፣ የካሳ አከፋፈል፣ የንብረት ክፍፍል፣ ወዘተ... ናቸው፡፡ እነዚህ ሕግጋት ሊሠሩ የሚችሉት መለኮታዊ አስተዳደር (Theocracy) ባለበት ቦታ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ የሕግ መጻሕፍትን ስናጠና እነዚህን ሦስቱን በመለየትና የትኞቹ ለእስራኤላውያን ብቻ እንደተሰጡና የትኞቹ ደግሞ ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዳላቸው በመረዳት መሆን አለበት፡፡

ሌላው እዚህ ጋር ሊታወስ የሚገባው ነጥብ ቢኖር አብዛኞቹ የመቅደሱ የአምልኮ ሥርዓቶች ክርስቶስ ኢየሱስን የሚያሳዩ መሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህ የትኞቹ በክርስቶስ ሕይወት እንደተፈጸሙ መመልከት ያስፈልገናል፡፡ ይህንን በሚገባ ለመረዳት የዕብራውያንን መጽሐፍ ማንበብ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡


ይቀጥላል...


ምንጭ:- www.ewnetlehulu.org




ወደ ቻናሉ ለመ🀄️🀄️ል፦ @Holy_scriptures
❤4
August 20, 2026 1K 9