ፕሮቴስታንት (Protestantism) ከ16ኛው ክፍለ ዘመን የአውሮፓ ተሐድሶ (Reformation) እንቅስቃሴ የመነጨ የክርስትና ዋነኛ ቅርንጫፍ ነው።
"ፕሮቴስታንት" የሚለው ቃል የመጣው "ተቃውሞ" ወይም "መቃወም" ከሚለው ቃል ነው። ይህ ስያሜ በዋነኝነት የተሰጠው በእንቅስቃሴው መጀመሪያ ላይ የነበሩ መሪዎች በወቅቱ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታዩትን ሥርዓቶች፣ ትምህርቶች እና ተግባራት በመቃወማቸው ነው።
መሠረታዊ አስተምህሮዎቹ (አምስቱ ሶላዎች):
ፕሮቴስታንትነት በአብዛኛው በአምስት ዋና ዋና መርሆዎች (ሶላዎች - Solas) ላይ የተመሠረተ ነው፦
1,መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ (Sola Scriptura):
የመጨረሻውና ብቸኛው ሥልጣን ያለው የሃይማኖት ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ እንደሆነ ያምናሉ። ከቤተ ክርስቲያን ትውፊት ወይም ከጳጳሳት ውሳኔዎች ይበልጣል ።
2,እምነት ብቻ (Sola Fide):
ሰው የሚጸድቀው ወይም የሚድነው መልካም ሥራዎችን በመስራት ሳይሆን፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባለው እምነት ብቻ እንደሆነ ያስተምራሉ።
3,ጸጋ ብቻ (Sola Gratia):
መዳን በሰው ጥረት ወይም ብቃት ሳይሆን፣ ከእግዚአብሔር የሚገኝ ያልተገባ ጸጋ ብቻ እንደሆነ ያምናሉ።
4,ክርስቶስ ብቻ (Solus Christus): በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው ብቸኛው መካከለኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ስለዚህ ወደ ሌሎች ቅዱሳን መጸለይ ወይም መማለጃ መጠየ፡ አያስፈልግም ይላሉ።
5,ክብር ለእግዚአብሔር ብቻ (Soli Deo Gloria):
ክብርና ምስጋና ሁሉ የተገባው ለፈጣሪ እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ ያምናሉ።
ማርቲን ሉተር
የፕሮቴስታንት እንቅስቃሴ ዋና መሪ ጀርመናዊው ካህንና የነገረ-መለኮት ምሁር የነበሩት ማርቲን ሉተር ናቸው። ሉተር የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን 'የንስሀ ደብዳቤ' ሽያጭን በመቃወም በ1517 ዓ.ም. 95 የተቃውሞ ጽሑፎችን በቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ላይ ለጥፏል።
ከዚያ ሪፎርሜሽን በኋላ ፕሮቴስታንትነት ወደ ብዙ የተለያዩ ቅርንጫፎች ተከፋፍሏል፤ ከእነዚህም ዋና ዋናዎቹ:
ሉተራን (Lutheran)
ሪፎርምድ (Reformed) / ፕሬስባይቴሪያን (Presbyterian)
አንግሊካን (Anglican) / ኤጲስ ቆጶሳዊ (Episcopal)
ባፕቲስት (Baptist)
ሜቶዲስት (Methodist)
አድቬንቲስት (Adventist)
ጴንጤቆስጤ (Pentecostal) - በአብዛኛው "ጴንጤ" የሚለው አጠራር በኢትዮጵያ ለፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ መጠሪያ ሆኖ ያገለግላል።
በኢትዮጵያ ደግሞ እንደ መካነ ኢየሱስ፣ ቃለ ሕይወት፣ ሙሉ ወንጌል፣ መሰረተ ክርስቶስ የመሳሰሉት አብያተ ክርስቲያናት የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ናቸው።