የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያስመዘገቡት የአንበሳ ባንክ ጥበቃ ሠራተኛ ማበረታቻ ተበረከተላቸው
#FastMereja | በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን ሰለዋ ወረዳ ደላ ከተማ በሚገኘው የአንበሳ ባንክ ቅርንጫፍ ለሰባት ዓመታት በጥበቃ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ሰይፈ ተስፋዬ ካሕሳይ፣ በ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ወስደው 320.25 ነጥብ በማምጣት ወደ ዩኒቨርሲቲ ማለፋቸውን ተክተሎ የባንኩ ሥራ አመራር ከፍተኛ ማበረታቻ መስጠቱን አስታወቀ።
የአንበሳ ባንክ የዳይሬክቶሮች ቦርድ፣ ማኔጅመንት እና ሠራተኞች በአቶ ሰይፈ ተስፋዬ ስኬት የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ የገለጹ ሲሆን፣ ለሠራተኛውና ለቤተሰቦቻቸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ባንኩ የአቶ ሰይፈን የትምህርት ጉዞ ለማገዝ እና የነበራቸውን የላቀ ጥረት ለማስቀጠል የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል፤
እንደ ባንኩ ማኔጅመንት ውሳኔ፣ አቶ ሰይፈ ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ትምህርታቸውን እስከሚያጠናቅቁ ድረስ የሚያስፈልጋቸውን ማንኛውንም ወጪ ባንኩ ሙሉ በሙሉ ይሸፍናል። ከዚህ በተጨማሪም ትምህርታቸውን በሚከታተሉበት ወቅት የቤተሰቦቻቸውን የኑሮ ሁኔታ ለማደገፍ ሲባል፣ አሁን የሚከፈላቸው ወርሃዊ ደመወዝ ሳይቋረጥ በየወሩ ለቤተሰቦቻቸው ገቢ እንዲደረግ ተወስኗል።
ሠራተኛው የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በተሳካ ሁኔታ አጠናቀው ሲመለሱም ባንኩ በተማሩበት የትምህርት መስክና በተገቢው የሥራ ዘርፍ ይመድባል፤ በቋሚነትም መድቦ እንደሚያሰራቸው ገልጿል።
ይህ እርምጃ ባንኩ ለሠራተኞቹ የትምህርት እድገትና ለላቀ ጥረት የሚሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ መሆኑ ተጠቅሷል።
54
10August 29, 2026 4.8K 3