አለን ኢትዮጵያ ኤክስፕረስ አዲስ የሜትር ትራንስፖርት መተግበሪያ አስተዋወቀ
#FastMereja I በሀገራችን እየተስፋፋ ባለው የዲጂታል የትራንስፖርት ሴክተር ውስጥ የደንበኞችን ደህንነት የሚያረጋግጥ እና ያልተጠበቀ ተጨማሪ ክፍያን የሚያስቀር አዲስ አሰራር ይዞ መምጣቱን አለን ኢትዮጵያ ኤክስፕረስ (Alen Ethiopia Express) አስታወቀ። ድርጅቱ በዛሬው ዕለት ባካሄደው የጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደገለጸው፣ መተግበሪያው ከሌሎች መሰል አገልግሎቶች ለየት የሚያደርጉትን ዋና ዋና የቴክኖሎጂ አሰራሮች እና የትራንስፖርት አማራጮች ይዞ ቀርቧል።
ከተካተቱት አዳዲስ አገልግሎቶች መካከል ተሳፋሪው ጉዞ ከመጀመሩ በፊት መነሻና መድረሻውን በመተግበሪያው ላይ በማስገባት የሚከፍለውን የመጨረሻ ዋጋ አስቀድሞ የሚያውቅበት የቋሚ ዋጋ (Fixed Pricing) አሰራር ዋነኛው ሲሆን፣ ይህም በትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት የሚፈጠርን ተጨማሪ ክፍያ የሚያስቀርና ደንበኞች የበጀት ወጪያቸውን አስቀድመው እንዲያቅዱ የሚያስችል ነው ተብሏል። ከዚህ በተጨማሪም ተሳፋሪዎች በመንገድ ላይ የሚያገኙትን የአለን አሽከርካሪ በቀጥታ በመያዝ በሜትር የመጠቀም አማራጭ ተመቻችቶላቸዋል።
በሌላ በኩል የተሳፋሪዎችን እና የአሽከርካሪዎችን ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የኦቲፒ (OTP – One Time Password) የማረጋገጫ ኮድ አሰራር መዘርጋቱ ተገልጿል። በዚህ አሰራር መሰረት አሽከርካሪው ጉዞ ከመጀመሩ በፊት በተሳፋሪው ስልክ ላይ የሚላከውን አጭር ማረጋገጫ ኮድ በመቀበል አፕሊኬሽኑ ላይ ማስገባት የሚጠበቅበት ሲሆን፣ ይህም የተሳሳተ ደንበኛ ወይም አሽከርካሪ እንዳይገናኝ በመከላከልና የሀሰት ትዕዛዞችን በመቀነስ በኩል አስተማማኝ ደህንነትን ይፈጥራል ተብሏል።
ሁለት አመታትን ያስቆጠረው አለን ባለፉት ስድስት ወራት የሙከራ ትግበራ ስራ ላይ እንደነበሩ ገልፀው በአሁኑ ወቅት 300 አሽከርካሪዎች ተመዝግበው ስራ እየሰሩ መሆኑን ገልጷል።
አለን ኢትዮጵያ ኤክስፕረስ ከትራንስፖርት አገልግሎት ባሻገር የቁሳቁስ ማድረስ (Delivery) አገልግሎት፣ በሚኒቫን፣ በኢቪ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች፣ በሞተር ብስክሌት እና በብስክሌት ጭምር የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ስራ ገብቷል።
ተጠቃሚዎች የ9290 አጭር የጥሪ ማዕከልን ወይም የሞባይል መተግበሪያውን በመጠቀም አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉ ሲሆን፣ ድርጅቱ ለተደጋጋሚ ተጠቃሚዎችና ለአሽከርካሪዎች የተለያዩ የማበረታቻ ሽልማቶችን እና የጉዞ ቅናሾችን ማዘጋጀቱንም አያይዞ ገልጿል።
4
1August 31, 2026 1.4K 1