የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት በሀገረ ስብከት ደረጃ ለ3ኛ ጊዜ… — የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት -EOTC GSSU — TG.ME

የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት በሀገረ ስብከት ደረጃ ለ3ኛ ጊዜ ሲያሰለጥናቸው የቆዩ ተተኪ መምህራንን አስመረቀ።

የሰ/ት/ቤቶች አንድነት  ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም

በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ለ5ቀናት በመንበረ ጵጵስና ቅድስት ልደታ ቤተ ክርስቲያን ለ3ኛ ጊዜ ሲሰጠው የቆየውን የተተኪ መምህራን ሥልጠና የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ በተገኙበት አስመረቀ።

ሥልጠናው ከ 9 ወረዳ ቤተ ክህነት የተውጣጡ 120 ያህል የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች የተካፈሉበት ሲሆን፣ ታች በወረዳ እና በአጥቢያ ደረጃ የሰ/ት/ቤቶችን አገልግሎት የሚያሳድግና  የሥርዓተ ትምህርት ትግበራውን የሚያሳልጥ መሆኑን የሀገረ ስብከቱ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ ክፍል ሓላፊ መጋቤ ሥርዓት ቀሲስ ዘነበ ብርሃኑ ተናግረዋል። ይህ የሀገረ ስብከት ሥልጠና በአዲስ አበባ ለሚደረገው የሀገር አቀፍ የአሰልጣኝ መምህራን ሥልጠና መመልመያ አንዱ መድረክ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሀገረ ስብከቱ ሰ/ት/ቤቶች አንድነት ተቀዳሚ ም/ሰብሳቢ መ/ር መኮንን አብዩ ናቸው።

ሥልጠናው የተሰጠው ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምርያ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት በተወከሉ መምህራን ነው። ይህ ሥልጠና በሀገር አቀፍ አንድነቱ በዘንድሮው ዓመት ሀገረ ስብከቶች እንዲያሳኳቸው ከሚጠበቁ እና እንደ ዕቅድ ተይዞ ከሚሠራባቸው የሥልጠና ማዕከላት  አንዱ እንደሆነ በምርቃት መርሐ ግብሩ የተገኙትና ሥልጠናውን የሰጡት፣ የሀገር አቀፍ ሰ/ት/ቤቶች አንድነት ሥርዓተ ትምህርት አስተባባሪ መ/ር ሚኪያስ ግዛቸው ገልጸዋል። አያይዘውም ሥልጠናው ሥርዓተ ትምህርት ትግበራ፣ የመምህራን ክህሎት ግንባታ፣ የክፍላተ ትምህርት ገለጻ ላይ ያተኮረ ሀገረ ስብከት አቀፍ ሥልጠና እንደሆነ ተናግረዋል።

በምርቃት መርሐ ግብሩ የሥልጠና ሪፖርትና የሀገረ ስብከቱን አንድነት የሥርዓተ ትምህርት ትግበራ አካሔድ እና ሥልጠናውን በተመለከተ 12 ያህል የአቋም መግለጫ በማውጣት እንዲሁም ሠልጣኞችን ለላኩ እና በሥልጠናው ለተሳተፉ ተተኪ መምህራን የምስክር ወረቀት በመስጠት ተጠናቋል።

የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የማኅበራዊ የትስስር ገጾችን ቤተሰብ ይሁኑ!

(የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት)

👉 Youtube

👉 Facebook

👉 Telegram

👉 Tiktok

👉  Website
❤9👍1
August 3, 2026 3.7K 5