በደቡብ ኦሞ አሪ ዞን ሀገረ ስብከት በሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ለአንድ ሳምንት ሲሰጥ የነበረው የተተኪ መምህራን ሥልጠና ተጠናቀቀ።
ነሐሴ 24/ 2018 ዓ.ም የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት
በደቡብ ኦሞ አሪ ዞን ሀገረ ስብከት በሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት በሀገረ ስብከቱ ከሚገኙ 7 ወረዳ ቤተክህነት ለተውጣጡ የሰንበት ትምህርት ቤት መምህራን ከነሐሴ 18-22 ሲሰጥ የነበረውን ሥልጠና የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ መንክራት ቆሞስ አባ ስምረተ አብ እሸቴ እንዲሁ የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ትምህርት ቤት ክፍል ሓላፊ መጋቤ ሰናያት መምህር ፍሬው አሰፋ በተገኙበት በታላቅ ድምቀት አስመርቋል።
ሲሰጥ የነበረው ሥልጠና በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሰጠ ባለው የሰንበት ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት አተገባበርና የማስተማር ሥነ ዘዴ ላይ ያተኮረ እንደሆነ ሥልጠናውን የሰጡት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምርያ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ሥርዓተ ትምህርት አስተባባሪ መምህር ሚኪያስ ግዛቸው ገልጠዋል።
የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ትምህርት ቤት ክፍል ሓላፊ መጋቤ ሰናያት መምህር ፍሬው አሰፋ በበኩላቸው ሀገረ ስብከቱ ባለው ርቀት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚከናወነው የመምህራን ሥልጠና ሠልጣኞችን ልኮ ማሰልጠን ባይቻልም በሀገረ ስብከቱ የዚህ የሥልጠና መድረክ ዓላማ የመምህራንን ግንዛቤ እና አቅም መፍጠርያ እና ማጎልበቻ መሆኑን ገልጠዋል። አያይዘውም ከዚህ ሥልጠና ጎን ለጎን በከተማዋ ጂንካ ለሚገኙ የሥርዓተ ትምህርቱ ትግበራ ባለ ድርሻ አካላት የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፣ የአብነት መምህራን፣ ሰበካ ጉባኤ ሓላፊዎችና ሰባኪያነ ወንጌል የሥልጠና መድረክ እንደተዘጋጀ ተናግረዋል።
በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ መንክራት ቆሞስ አባ ስምረተ አብ እሸቴ ሰልጣኝ መምህራን በሰለጠኑት ሥልጠና የእውቀትና የአመለካከት ለውጥ በሚያከናውኑት አገልግሎት ሁሉ እንዲያመጡ፣ መልዕክትን በማስተላለፍ ለሠልጣኞች የምስክር ወረቀት ተሰጥቶ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል።
በተያያዘ ነሔሴ 23 በከተማዋ ጂንካ ለሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፣ የአብነት መምህራን እና ሰባኪያነ ወንጌል ለሰንበት ትምህርት ቤት ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደጊያ ሥልጠና ተሰጥቷል። በመርሐ ግብሩ ፍጻሜም የሀገረ ስብከቱ ስራአኪያጅ መልአከ መንክራት ቆሞስ አባ ስምረተ አብ እሸቴ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ግንዛቤያችንን በማስተካከል፣ለሰንበት ትምህርት ቤት ልዩ ትኩረት በመስጠት፣ የነገውን ትውልድ ላይ እንስራ፣ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጂንካ
የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የማኅበራዊ የትስስር ገጾችን ቤተሰብ ይሁኑ!
(የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት)
👉 Youtube
👉 Facebook
👉 Telegram
👉 Tiktok
👉 Website
6
4
1August 30, 2026 2.6K 1