የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ ጋር… — የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውስንል ECGBC — TG.ME

የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ ጋር በመተባበር በማኅበራዊ ሚዲያና ብሮድካስት አጠቃቀም ላይ ሥልጠና ሰጠ።

ይህ ሥልጠና የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም ከማኅበራዊ ሚዲያ እና ከብሮድካስት አገልግሎት ሥራዎች ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ በካውንስሉ ሥር ለሚገኙ የወንጌል አማኞች ሚዲያዎች በሙሉ የተሰጠ ነው።

የፍትሕ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አሰፋ መብራቱ እንደገለጹት ሥልጠናው የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃዎች ከሕግ አንጻር የሚያስከትሏቸውን ችግሮች ለማየት እና ለዚህም የመፍትሔ ሐሳብ ለማስቀመጥ ያለመ ሲሆን፣ እነዚህን ችግሮች እንዴት መከላከል እንደሚቻል ለመመልከት የተዘጋጀ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል የሕግ ክፍል ኃላፊ ወይዘሪት መንበረ አንድነት በበኩላቸው የወንጌላዊያን ሚዲያዎች ከሕግ አንጻር ምን ያህል ያውቃሉ? በሕጉስ መሠረት እየሠሩ ነው? የሚለውን ለማስገንዘብ ጭምር ሥልጠናው መዘጋጀቱን አንስተዋል።አክለወም ካውንስሉ በተጨማሪም ከሕግ አንጻር የተለያዩ ሥልጠናዎችን በቀጣይነት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ የሕግ ሥርጸትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት አካዳሚክ ዓቃቤ ሕግ አቶ ሙሴ ባዬ ሥልጠናውን የሰጡ ሲሆን፥ ከተሳታፊዎች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

በስልጠናው ላይ የተሳተፉት ሰልጣኞች በቆይታቸው እጅግ ጠቃሚ እና ጥሩ ጊዜ እንደነበራቸውም ገልጸዋል።ከዚህ ስልጠና የቀሰሙትን እውቀትና ክህሎት በስራቸው ላይ በተግባር እንደሚያውሉትና ውጤታማ እንደሚሆኑ ሙሉ እምነት እንዳላቸው አስታውቀዋል።

ለኢቫንጄሊካል ዜና ቤተልሔም ደረጀ
❤12👏2😭1
August 11, 2026 2.2K 3