ውቅያኖሱ ጨዋማ መሆኑን ለማወቅ . . . “ውቅያኖሱ ጨዋማ መሆኑን ለማወቅ ሙሉውን ውቅያኖስ መጠጣት… — Dr. Eyob Mamo — TG.ME

ውቅያኖሱ ጨዋማ መሆኑን ለማወቅ . . .

“ውቅያኖሱ ጨዋማ መሆኑን ለማወቅ ሙሉውን ውቅያኖስ መጠጣት አያስፈልግም፤ አንድ ጉንጭ ብቻ ቀምሰህ እወቀውና መንገድህን ቀጥል”፣ ይባላል፡፡

ይህ አባባል ከሰዎች ጋር ግንኑነትን ስንመሰርት ምልክቶችን ማየትን፣ ከልምድ መማርን እና መቼ በግንኙነቱ መቀጠል እንዳለብን እና መቼ መራቅ እንደሚገባን የሚገልጽ አባባል ነው።

አንድ ሰው ሆን ብሎ ከከዳችሁ፣ አስቦበት ካታለላችሁ፣ ደጋግሞ ከዋሻችሁ፣ በተንኮል ከተጠቀመባችሁ፣ እና ካለማቋረጥ የሚቆጣጠራችሁ ከሆነ ይህንን ችግር ለማረጋገጥ ተመሳሳይ ነገር እስከ 10 ጊዜ ደጋግሞ እስኪያደርግባችሁ መጠበቅ አያስፈልጋችሁም::

አንዳንድ ጊዜ አንድ ክስተት የሰዎችን የማይለወጥ ባህሪይ የማወቂያ ምልክት ይሆናል፤ ያው ነገር ደጋግሞ መከሰቱ ደግሞ ንድፍ (pattern) ሊታይና ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል፡፡

የሰዎችን ቃላት ብቻ ሳይሆን ተግባራቸውንም ተመልከቱ፡፡ የሚነግሯችሁ ሌላ፣ የሚተገብሩት ሌላ ሲሆን ያንኑ የክህደት ተግባራቸውን እየተጎነጫችሁ መኖር የለባችሁም፡፡
አንድ ሰው “እወድሃ/ሻለሁ” የሚለው ቃል በድርጊቱ ካልተደገፈ፤ “እመነ/ኚኝ” የሚለው ንግግሩ በክህደት ተግባሩ ካፈረሰው ቃሉ ብቻ በቂ አይደለም ማለት ነው።
በይቅርታ የምታልፉን የአንድ ጊዜ ስህተትና በሰዎቹ ላይ የምታዩትን የባህሪይ ሁኔታና ድግግሞሾች ለዩ፡፡

አንዳንድ ጊዜ እውነቱን አውቀን እንኳን መቀበል ስለማንፈልግ ተጨማሪ ማስረጃ እንፈልጋለን።

“ምናልባት ይለወጣል።”

“ምናልባት ይህ የመጨረሻው ጊዜ ነው።”

“ምናልባት እኔ ተሳስቻለሁ።”

“ምናልባት ብወደው ይለወጣል።”

ነገር ግን የአንድን ሰው እውነተኛ ባህሪ በተስፋው ሳይሆን በተደጋጋሚ በሚያሳየው ድርጊት መለየት ይኖርባችኋል።

ስለዚህ ምን እናድርግ?

1.      ይቅርታ ማድረግን እና ድንበር (የቀይ መስመር) ማበጀትን አታምታቱ

ለሰዎች ይቅርታ አድርጉ፣ የሚጣስ ክልላችሁን ግን በሚገባ አስምሩ፡፡ ይቅርታ ማለት ድንበር የሌለውና ሰው መጫወቻ መሆን አይደለም።

2.     ትእግሥትን ራስን ለጉዳት ከማጋለጥ ጋር አታምታቱ

ሰዎችን ታገሱ፣ ነገር ግን የማይቀለበስ ጉዳት እስከሚደርስባችሁ ድረስ አትጠብቁ፡፡ ትእግስት ማለት ራስን ለጥፋት ማጋለጥ ማለት አይደለም፡፡

3.     ከሰው መራቅን እና ጥላቻን አታምታቱ

ሰዎችን አትጥሉ፣ ነገር ለህልውናችሁ አደጋ ከሚሆን ሁኔታ ራሳችሁን ጠብቁ፡፡ ከጎጂ ሰው ርቀታችንን መጠበቅ ማለት በጥላቻ መሞላት ማለት አይደለም፡፡

አንዴ ባያችሁት ባህሪይ ወይም ተግባር ምክንያት ሰዎችን አትፈርጇቸው፡፡ ሆኖም፣ የምታዩትን የባህሪይ ድግግሞሽ በሚገባ በማጥናትና በመመርመር ተገቢውን ውሳኔ ውሰዱ።

https://t.me/Dreyob

https://m.youtube.com/user/naeleyob623

https://www.facebook.com/Dr-Eyob-Mamo-1050816404958639/
Telegram
Dr. Eyob Mamo
Life skill development! You can contact me @DrEyobmamo
❤43👍34🔥4🎉1
August 26, 2026 8.5K 4 35