ዋናው ሀሳቡ ነው እንጂ ቃላቱ አይደለም i ክፍል 2 አንድ ቀን ታዲያ ሙሉ በሙሉ መንገዴን የሚቀይር ነገር… — Daniel Wodajo — TG.ME

▫️ዋናው ሀሳቡ ነው እንጂ ቃላቱ አይደለም i

ክፍል 2

አንድ ቀን ታዲያ ሙሉ በሙሉ መንገዴን የሚቀይር ነገር ተከሰተ
ለኔ - Breakthrough Moment

በሰዓቱ ከማህበራዊ ሚዲያ አልፈን የራዲዮ ኘሮግራም ማዘጋጀት ጀምረናል። ኘሮግራሙ የሚተላለፈው ደግሞ ላይቭ ነበርና ስለምናነሳዉ ሀሳብ ከባልደረቦቼ ጋር ብዙ ተወያይተን ገባን። አኔ ግን ከሀሳቡ እኩል አዕምሮዬን ሙሉ የተቆጣጠሩት “አማርኛ አትችልም ፣ ንግግርህ አይስብም” የሚሉት ቃላት ናቸው ።

ሰላምታ ሰጥተን ገና ኘሮግራሙ እንደተጀመረ ትንሽ እንደተናገርኩ ያልጠበቅኩት ነገር ተከሰተ!

በጣም ደነገጥኩ እንደዛ ቀን ደንግጬ የማውቅ አይመስለኝም ተንተባተብኩ ፣ አፌ ተሳሰረ ፣ ቃል ማውጣት ከበደኝ ምንም ማድረግ አልችልም ዋናው አዘጋጅ እኔ ብሆንም ለባልደረቦቼ ኘሮግራሙን እንዲቀጥሉ ምልክት ሰጥቼ እኔ ዝም አልኩ።

እነሱ እየተናገሩ በድንጋጤ ውስጥ ብሆንም “ዳንኤል እዚህ ደረጃ እስክትደርስ ምን ሆነሃል ፣ ለዚህ ነገር ቶሎ መፍትሄ ማግኘት አለብህ! ዛሬውኑ!” ብዬ በቁጣ ራሴን እየገሰፅኩት ነበር።

ፕሮግራሙ እንዳለቀ ጊዜ ሳላጠፋ በፍጥነት ወደቤት ሄድኩኝ

የሰው ልጅ ከቆረጠ የሚፈልገውን እንደሚያገኝ ከተረዳሁባቸው ቀፅበቶች አንዱ ይሄ ነው . . .

መፅሐፍ ማገላበጥ ጀመርኩ (ያዉ እንግሊዘኛ) ብዙም ሳልቆይ Psycho-Cybernetics የሚባል መፅሐፍ ላይ አንድ ሀሳብ ትኩረቴን ሳበው።

‘Stutter’ የሚያደርጉ ወይም የሚንተባተቡ ሰዎች አንዱ ምክንያት ልጆች እያሉ ወይም ገና አፍ ባልፈቱ ሰዓት ለመናገር ሲዘገዩ አሊያም ሲቸገሩ ከቤተሰብ በተደጋጋሚ የሚሰነዘርባቸው የተለያዩ ቃላቶች ናቸው።

ለምሳሌ- “ይሄ ልጅ ኮልታፋ ነው፣ በስርዓት መናገር አይችልም ፣ ተብታባ ነዉ የሚሉ ቃላት” ይላል

መልሱን አገኘሁት ተነስቼ በደስታ ዘለልኩ በተደጋጋሚ አንብቤዋለው፣ ለብዙ ሰዎችም አስተምሬዋለው፤ እንዴት እስከአሁን እኔ ተሸወድኩ እንጃ ለሆነ ነገር ራሴን መውቀስ አልወድም ቀጥታ ወደ መፍትሄው ሄድኩ

“ንግግሬ እያማረ ነው ፣ አንደበተ ርቱዕ እየሆንኩ ነው ፣ የፅሁፍ ችሎታዬ በየጊዜዉ እያደገ ነው ፣ ቃላቶቼ ለሰዎች ይማርካሉ” እነዚህ ቃላቶች በትልቁ ፃፍኳቸዉ ፣ በተደጋጋሚ ፣ በየቀኑ ለራሴ መንገር ጀመርኩ።

ከጊዜያት በኋላ ስሜቴ መቀየር ጀመረ ያኔ ተግባሬም ተለወጠ የገዛኋቸውን አማርኛ መፅሐፍት ደስ እያለኝ ማንበብ አይደለም ሌላ ብዙ ጨመርኩ ፣ የፅሁፍ ችሎታዬን ለማዳበር በየቀኑ መለማመድ ጀመርኩ (ልምምዴ እንደቀጠለ ነው) ፤ መፃፍ በጣም ከምወዳቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ ሆነ።

እሱ ብቻ ግን አይደለም አማርኛ መፅሐፍትን ማንበብ ከቃላት በላይ ብዙ ውለታ ዋለልኝ ከሀገሬ ደራሲዎች ጋር አስታረቀኝ ከሀገሬ ታሪክ ፣ ህዝብ ጋር ይበልጥ አዋደደኝ ፤ ሀሳቦቼን የምገልፅበት መንገድ ብቻ ሳይሆን ሀሳቦቼም መቀየር ጀመሩ።

ቃላት ሀይል አላቸው። በምንናገራቸው ቃላት ራሳችንን ልናስር እንዲሁም ነፃ ልናወጣ እንችላለን። የምንናገራቸው ቃላት ስሜታችንን ይቆጣጠራሉ፣ ስሜታችን ድርጊታቸንን ይቆጣጠራል ፣ ድርጊታችን ደግሞ ውጤታችንን ይወስናል።

አመሠግናለው !

ስለ ‘ተግባር’ የስልጠና አልበም
መረጃ ለማግኘት 👇

www.DanielWodajo.com
👍46👏2
August 10, 2026 8.9K 9