ዋናው ሀሳቡ ነው እንጂ ቃላቱ አይደለም i ክፍል 1 የሙሉ ጊዜ ተማሪ በነበርኩ ሰዓት ከትምህርት ቤታችን ሰቃይ… — Daniel Wodajo — TG.ME

▫️ዋናው ሀሳቡ ነው እንጂ ቃላቱ አይደለም i

ክፍል 1

የሙሉ ጊዜ ተማሪ በነበርኩ ሰዓት ከትምህርት ቤታችን ሰቃይ ከሚባሉ ተማሪዎች መሃል አንዱ ነበርኩ። ታዲያ በሌሎች ትምህርቶች ላይ ሁሌም ከፍተኛ ውጤት ባመጣም የቋንቋ ትምህርቶች ላይ ማለትም አማርኛ ፣ እንግሊዘኛ ልጅ እያለን ደግሞ ፈረንሳይኛ እንማር ነበር ውጤቴ መጥፎ ባይባልም እንደሌሎቹ አይሆንልኝም።

ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ሀሳቡን ከየት እንዳመጣሁት ፣ ማን እንደሰጠኝ ባላውቅም ቋንቋ እውቀት አይመስለኝም ነበር ፤

አማርኛ ደግሞ አፍ መፍቻ ቋንቋዬ ስለነበርና አውቃለው ብዬም ስለማስብ ይሁን ተገቢውን ትኩረት አልሰጠውም።

መፅሐፍት ማንበብም ቢሆን ከት/ት መፅሐፍት ባለፈ አልፎ አልፎ ይሄንማ ማንበብ አለብህ ብለው ጓደኞቼ ከሚጠቁሙኝ እና ብዙ ከሚወራላቸው መፅሐፍቶች ውጪ ብዙም የማንበብ ልማድ አልነበረኝም።

በእነዚህ እና መሰል ምክንያቶች በተለይ ከአማርኛ ትምህርት ጋር ሳልስማማ 12ተኛ ክፍልን ጨርሼ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በኢንጂነሪንግ ተቀላቀልኩ።

እንደኔ ሀሳብ ከዛ በኋላ ማንም ግጥም ፃፍ ፣ ሥነ-ፅሁፍ አዘጋጅ አይለኝም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አማርኛ ትምህርትን እገላገለዋለው ( በምወደው ነገር እንደሚመጣብኝ መች አወቅኩ )

በመሃል ብዙ ነገር አለፈና ተመርቄ ከወጣው ከአንድ አመት ተኩል በኋላ ‘Inspire Ethiopia’ን በአጋርነት መሰረትኩኝ።

‘Inspire Ethiopia የተለያዩ አነቃቂ እና አስተማሪ ሀሳቦችን ለሰዎች በዋናነት በዩቲዩብ ቪዲዮ ለማድረስ ያቋቋምነዉ ድርጅት ነበር።

ታዲያ ቪዲዮዎቹን ለማዘጋጀት ሀሳቦቹን በእንግሊዘኛ ከተዘጋጁ መፅሐፍት ፣ ቪዲዮዎች እንዲሁም ስልጠናዎች ብናገኝም በአማርኛ ነውና የሚቀርቡት ለዛ ደግሞ ቀድሞ ስክሪኘት ማዘጋጀት ግድ ይላል። (የሸሸሁት ሥነ-ፅሁፍ ባላሰብኩት መንገድ ተከትሎኝ መጣ)

ምንም ምርጫ የለም ስራውን እወደዋለው እያማጥኩም ቢሆን ባለኝ አማርኛ ማዘጋጀት ጀመርኩ።

ከጊዜያት በኋላ ግን ያለኝ አማርኛ አልበቃ አለ ብዙ ሰዎች አስተያየት መሰንዘር ጀመሩ “ዳኒ ሀሳብህ ጥሩ ነዉ አቀራረብህን ግን አስተካክል ፣ አማርኛህ አይስብም ፣ እውቀት እንዳለህ ታስታው ቃለህ አገላለፅ ግን አትችልም ፣ ቃላት አጠቃቀምህን አስተካክል ፣ ንግግር አትችልም” መባል ጀመረ

መጀመርያ ያልሰራሁበትን አሁን ከየት ላምጣው ስለዚህ እንደለመድኩት ቆንጆ ማምለጫ አዘጋጀው

“ ዋናዉ ሀሳቡ ነው እንጂ ቃላቱ አይደለም! ”

ከጊዜያት በኋላ ግን አጠገቤ ካሉ እና ፣ በተለያየ አጋጣሚ ከሚያውቁኝ ሰዎችም ተመሳሳይ አስተያየት መምጣት ጀመረ ስለዚህ ዝም ብዬ ማለፍ አልቻልኩም።

መፍትሄው ብዙ አማርኛ መፅሐፍትን ማንበብ ፣ የፅሁፍ ችሎታን ለማዳበርም ትኩረት ሰጥቶ በቀን የተወሰነ ሰዓት መለማመድ እንደሆነ ስለተነገረኝ

አማርኛ መፅሐፍትን ገዛው ፣ ችግሩ ማን ያንብባቸው ገና ለማንበብ አስቤ መፅሐፍቶቹን ስገልፅ በተደጋጋሚ የሰማሁት እና ያነበብኩት “አማርኛ አትችልም ንግግርህ አያምርም” የሚሉ ቃላቶች ናቸው አዕምሮዬ ላይ የሚመጡት ፣ ማንበብ አቃተኝ።

በዛ ሰዓት ትክክለኛ መፍትሄ ከመስጠት የለመድኩትን ራሴን ማታለል ቀጠልኩ ፤ “አማርኛ መፅሐፍ አነበብኩ አላነበብኩ ሲጀመር የኔ ስራ ‘Personal Development‘ ማሰልጠን ነው ለሱ ደግሞ በቂ እውቀት ከእንግሊዘኛ መፅሐፍትና ስልጠናዎች አገኛለው።”( አሁን ሳስበው የነበርኩበት ሁኔታ ለራሴም ያስቀኛል !)

ታዲያ እኔ እውነታውን ብሸሸውም ከጊዜያት በኋላ ከጓደኞቼ ጋር ሁላ ቁጭ ብዬ ሳወራ አማርኛዬ ገብቷቸው ይሆን የምለውን ይረዱኝ ይሆን መጠራጠር ጀመርኩ ፣ ሰው ሁሉ በአማርኛዬ የሚያሾፍ እየመሰለኝ መጣ ጭራሽ አፍ መፍቻ ቋንቋዬም አልመስል አለኝ ።

ምን ማድረግ እንዳለብኝ ሊገባኝ አልቻለም ፤ ብዙዎችን የሚቀይር ሀሳብ ይዤ ለእኔ የሚሆን መፍትሄ አጣው። (የአባይን ልጅ ውሃ ጠማት ነው ነገሩ)

አንድ ቀን ታዲያ ሙሉ በሙሉ መንገዴን የሚቀይር ነገር ተከሰተ
ለኔ - Breakthrough Moment

ክፍል 2 ይቀጥላል . . .

ሰናይ ቀን ተመኘሁ !
ዳንኤል ወዳጆ
@Daniel_Wodajo
👍34👏3
August 10, 2026 8.4K 14