ባንዳነት አያሸንፍም፤ ምከሩ፤ ተመካከሩ!
እየተፈፀመብን ያለው በደል እንደሕዝብ በአማራነታችን መሆኑ ታውቆ ያደረ ነው። የጀመርነው የትግል ጉዞም በዚህ አውድ የተቃኘ ሆኖ ግስጋሴው ቀጥሏል። ሆኖም ግን ከፊሎቹ በአንድ በኩል ከፍርሃት የተነሳ በጉዞ ላይ ቁና ቁና እየተነፈሱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በስርአቱ ለየግላቸው በሚጣልላቸው የነብስ አድን ፍርፋሪና ለወደፊቱ ቃል በተገባላቸው መናኛ ጥቅማጥቅም እየጎመዡና ምራቃቸውን እያዝረበረቡ በየፌርማታው የወረዱ መሆኑ ይታወቃል።
ከመውረዳቸውም ባለፈ ወቅት እየጠበቁ ስርአቱ በሚያቀብላቸው መጋዝ እየገዘገዙ የምንጓዝበትን አማራዊ ሀዲድ ሊበጥሱ መከራቸውን ሲበሉ ይታያል። ይሔን ድርጊታቸውን ልማድ ወደማድረግ ስለተሸጋገሩ የውሸት ተራራ ሲከምሩ ሰው ምን ይለናል የሚል ይሉኝታም ማግኘት አልቻሉም። ሁሌም የሚደክሙት ቢያንስ ሌላውንም ጎትቶ የመጣል ውጤትን ለማግኘት ነው። ይህ የጥላቻ፣ ቅናት፣ ... ስሜት የሚፈጥረው ራስን የሚገድል መርዝ መሆኑ ነው። የውሸት ተራራቸው በስናፍጭ ታክል የእውነት ቅንጣጢት በደቂቃዎች እንደሚናድም ማሰብ ተስኗቸዋል። በቤተሰባዊ ምክር/ምክክር ከመታረም ይልቅ መላውን ቤተሰብም በውሸት ስሜት ኮርኩሮ በማሰባሰብና ወደ ጎጥ ንቅናቄ በማሳደግ የጎጥ ምሽግ ለመገንባት ሌትተቀን መከራቸውን ያያሉ። በተሳሳተ መንገድ እየዳከሩ መከራን ከመብላት ይልቅ አስተሳሰብን ማስተካከልና ወደ ተገቢው ሰልፍ መመለስ አይቀልም ነበር ወይ፤ ከሒደትም ሆነ ከውጤት አኳያ?
"ከአፈርሁ አይመልሰኝ" የውሸት ምክንያትና የስህተት መንገድ የትም አያደርስም!
ምከሩ፤ ተመካከሩ፤ ባንዳነት አያሸንፍም!
እነዚህ ለየግላቸው ዛሬ የሚጣልላቸውን ፍርፋሪና ለወደፊቱ አንጋጠው የሚጠብቁትን ድርጎ የአማራ ሕዝብ እየከፈለው ካለው ዋጋ እጅግ በልጦባቸው የምናገኛቸው ባንዳዎች ናቸው። የባንዳነት ትልቁ የስኬት ደረጃው መፈተን መቻሉ ነው። መጨረሻው ግን እንደአቧራ እየበነነ መጥፋት ነው። ክፋቱ ደግሞ በምርኩዝነት የተደገፉትንም አብሮ የሚያኮሰምን መሆኑ ነው። በዚህ ዘመን በምንም አውድ የዛሬን የባንዳነት ሚና ነገ በአርበኝነት ተረክ መተካት የሚያስችል አቅም ማግኘት ፈፅሞ አይቻልም። ከወረዱት ጋር መውረዱ መመለሻና መውጫ የሚያሳጣ አረንቋ ነው። ስለዚህ ራስንም ሆነ ሌላውን ከዚህ መንገድ መታደግ ነገን ማሳመር ነው። ምክንያቱም ስርአቱ በዚህ የሚድን እንዲሁም የአማራ ሕዝብ የድል ጉዞ በዚህ የሚሰናከል አይደለም።
ምከሩ፤ ተመካከሩ፤ ባንዳነት አያሸንፍም!
በአጠቃላይ ከዚህ የተሻለ ደረጃ ላይ የመገኘት አቅም የነበረው ቢሆንም የትውልዱ ግስጋሴ ይበል የሚያስብል ነው። የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች በወጉ እየተጋፈጠ ነው። እንደትውልድ የሚደረገውን አማራዊ መንገድ የሚያስቆመው ምድራዊ ኃይል አለመኖሩን መገንዘብና ማስገንዘብ ተገቢ ጉዳይ ነው። ኃይላችንም ሆነ ድላችን ያለውም አማራነታችን ላይ ነው። ስለአማራነታችን ደግሞ ትላንትና ዛሬ በአማራነት ቆመን በተግባር እንዳሳየነው ሁሉ ነገም እንቀጥላለን። በሌላውም ሆነ በባንዳው በየጊዜው የሚያጋጥመን ፈተና የሚመነጨው ከአማራዊ ፅናታችን ነው። በመሆኑም የጉዞው ማቆሚያ ድል ብቻ ነው። ድሉ ደግሞ አማራዊ ህልውናን አረጋግጦ ነፃነት፣ ርትዕና ፍትሕ የሰፈነበት ስርአት በጋራ መገንባት ነው።
#አማራዊ_አይበገሬነት
#AmharaResilience
@followers
7
1August 18, 2024 5.2K 1