ድርጅት ምስረታ እና ተያያዥ ጉዳዮች
(በድጋሚ የተለጠፈ)
~ ~ ~
ድርጅት ምስረታ በድጋሚ አጀንዳ እየሆነ ነው። እንደ ቀዳሚው ሙከራ ይኼም የመጨረሻው አይደለም። ስለዚህም አሁንም በውጤቱ ሳይሆን በሂደቱ ላይ እናተኩር።
ጠንካራ አደረጃጀት የሚመሰረተው በሂደቱ ውስጥ በሚወሰዱ ውሳኔዎች በስተጀርባ መርህ እና ምክንያታዊነት የተከተሉ ብያኔዎች ሲሰጡ ነው። በተረፈ የአንድነት ሂደቱ መጀመሩ በራሱ ወሳኝ ምዕራፍ ለመከፈቱ በቂ ማሳያ ነው።
ምን አይነት አደረጃጀት ?
ጥላ ወይስ ድርጅት !?
በትግል ውስጥ የድርጅት ዋነኞቹ መሠረታዊ ችግሮች የሚከሰቱት አመሠራረት ላይ ነው። በአመሠራረት የሚሰሩ ስህተቶች ሰርሳሪ ተረከዞች ሆነው በኋላ ላይ ለውድቀት ይዳርጋሉ።
በአመሠራረት ወቅት ከሚሰሩ ስህተቶች መሀከል ዋነኛው ደግሞ ከግለሰብ ልዩነት የሚሻገሩ ሀልዮታዊ /የነቢብ/የሀሳብ ልዩነቶች ባልተታረቁበት አለያም ብያኔ ሳያገኙ የሚፈጠሩ ጥምረቶች ናቸው። እነዚህ ጥምረቶች አንድም በአቅላይነት፣ አንድም ጉዳዩን በሚገባ በመጠን ባለመረዳት፣ አንድም በችኮላ ወደ መፍትሔ በመሮጥ እንዲሁም አፈጻጸም መሳለጥን ከመዋቅራዊ ተግዳሮቶች በማስበለጥ እና ጊዜያዊ አሸናፊነትን ለመቆናጠጥ የሚወሰዱ ውሳኔዎች ናቸው። . . .
በዚህ አግባብ ውሳኔዎች ሲወሰኑ ብዙ ጉድለቶች አሉ፤ ከነዚህ መካከል በቂ የፖለቲካ ተዋስኦ አለመደረግ፣ የነባር ልዩነቶች መነሻቸው እና አይነታቸው በግልጽ አለመለየት፣ እንዲሁም ያለፉ ጉዞዎች ላይ የጋራ ግንዛቤ አለመወሰድ እና ቀጣይ ርዕዮተ አለማዊ መስመር የሚያስይዙ ብያኔዎች ሳይሰጡ ውሳኔዎች መወሰናቸው ትልቅ ጉድለት ነው።
እነዚህን ጠቃሚ የውስጣዊ የፖለቲካ ትግል መሠረታዊያን ያላማከለ ውሳኔ፣ የትግሉ መሪዎች ጊዜያዊ ስምምነት ከመሆን ባለፈ ዘላቂነት አይኖረውም። በተለያዩ ምክንያቶች መሠል የመሪ ቡድን ጥምረቶች ቢቀጥሉ እንኳ መሪ ቡድኖች በተናጠል እንዲሁም በጋራ ከማህበራዊ መሠረታቸው ጋር ልዩነት ውስጥ መግባታቸው አይቀሬ ነው። እንዲሁም እነዚያ በደንብ ያልጠሩ የቤት ስራዎች በትግሉ ሂደት ከወታደራዊ ድል በፊትም ሆነ በኋላ ውስጣዊ ችግር በመሆን እራሳቸው የህልውና ስጋት መሆናቸው አይቀሬ ነው።
#እናም በትግላችን ውስጥ ያሉ መሪ ቡድኖች አንድ ድርጅት ለመፍጠር የሚያደርጉት ሂደት ተገቢው #ውስጣዊ_ፖለቲካዊ_ትግል ሊካሄድበት ይገባል።
የፖለቲካ ትግሉም የመንገድ፣ የሀሳብ እና የራዕይ ግልጽነት መፍጠር መቻል አለበት። ከተማከለ መዋቅር እና አፈጻጸም በፊት የራዕይ አንድነት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።
ለዚህ እንዲያግዝ ድርጅት የመፍጠር ትግሉ #ሂደቱን የጠበቀ መሆን አለበት። ይህም ሲባል አንድ ወጥ ድርጅት ከመፍጠር በፊት የጋራ ጥላ የሚሆን ተቋም መገንባት ይቻላል። ይህም ድርጅት ምስረታ ወቅት የሚኖሩ ክፍተቶችን በሂደት ለመሙላት ያግዛል። በተጓዳኝ ደግሞ የድርጅታዊ አንድነት ጉዞ ውስጥ መነሳት ያለባቸው ጉዳዮች ተነስተው በዚያ ዙሪያ አስፈላጊውን ትግል ለማድረግ እና የጋራ አቋም ይዞ በስምምነት ወደ ድርጅት ምስረታ ለመሄድ #መሸጋገሪያ_መደላድል ሆኖ ያገለግላል። በሂደቱ መጥራት ያለባቸው ጉዳዮች ላይ ግልጽነት ተይዟ አቋም ከተወሰደ በኋላ ጥላ የነበረውን ተቋም ወደ አንድ የጋራ ድርጅትነት ያድጋል።
በድርጅት ምስረታ ሂደቱ . . .
ርዕዮተ አለማዊ ጥራት እና አላማ መር ክርክሮቹ በምንተ ዕፍረት አለያም ቅያሜ ፍራቻ አይቆሙም።
ከአማራ ብሄረተኝነት ያፈነገጠ መስመር፣ ጓዳዊ ትምምን' ን የሚያፈርስ አንጃነት እና ተለጣፊነት ፍጹም ተቀባይነት እንደማይኖራቸው ግልጽ ሊሆን ይገባል።
ዋነኞቹ የአማራ ትግል መሠረታዊያን ፦
ጥያቄው ~ የህልውና እና የፍትህ ነው፣
ዕሳቤው/መስመሩ ~ አብዮታዊ የአማራ ብሄረተኝነት ነው፣
መንገዱ/ስትራቴጂው ~ ህዝቡ እና መሬቱ ላይ መትከል ነው።
አንዱን የአማራ ትግል በሦስት የጠመዱ መሠረታዊያን ውስጥ ሆነን የትኛውንም ሀሳብ በአማራዊ ወንድማማችነት አስተናግደን፣ መወያየት እና መከራከር እንችላለን። ከዚህ የወጣውን ግን በሀሳብ ልዩነት ደረጃም ቢሆን አይስተናገድም።
ይኸው ነው።
#AmharaRevolution
4
1
1September 16, 2024 3.1K 1