“በመሳሪያ ምንግዜም ማሸነፍ አይቻልም” - ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርኣያ
*****
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከ4,000 በላይ ተመካካሪዎችን በማሳተፍ ያካሄደውን ታሪካዊ መድረክ ሲያጠናቅቅ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የሀገራችን ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ሊያገኙ የሚችሉት በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ንግግር እንጂ በሃይል አለመሆኑን አስምረውበታል።
ፕሮፌሰር መስፍን "በመሳሪያ ምንጊዜም ማሸነፍ አይቻልም፤ ችግሮቻችን የሚፈቱት ከተነጋገርን እና ከተደማመጥን ብቻ ነው" በማለት ተሳታፊዎች ወደየአካባቢያቸው ሲመለሱ የሰላም አምባሳደር እንዲሆኑ አሳስበዋል።
መድረኩ የግለሰብ ወይም የቡድን ፍላጎት ሳይሆን የእኛነት እና የጋራነት ማሳያ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰሩ፣ ምክክሩ ችግሮችን የመፍታት ጅማሬ እንጂ ማብቂያ አለመሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም "ከሀገሬ ምንጊዜም አልኮበልልም" በማለት ቀሪ እድሜያቸውን ለኢትዮጵያ ሰላም ግንባታ እንደሚሰጡ በግላቸው ቃል ገብተዋል።
የጉባኤ መጠናቀቅ የአዲስ ምዕራፍ ጅማሮ መሆኑን ፕሮፌሰር መስፍን በንግግራቸው ጠቁመዉ ተመካካሪዎች በቆይታቸው ያነሷቸው አጀንዳዎች እና ያሳለፏቸው ውሳኔዎች ወደየመጡበት ክልሎች እና ከተማ መስተዳድሮች ተመልሰው እንደሚላኩ ገልጸዋል።
ከዚህም በመነሳት ተሳታፊዎች ያገኙትን እውቀት እና ልምድ መሰረት በማድረግ በየክልላቸው ሰፊ የክልል ውስጥ የምክክር መድረኮችን እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ክልሎች እርስ በእርሳቸው የሚወያዩበትን መድረክ እንደሚመሩ አብራርተዋል።
#ምክክር #ኢትዮጵያ