Part 3 ምናልባት አንድ ልዩ ምሳሌ ልዩነቱን እንድንረዳ ያስችለናል፡፡ አንድ ባል ሌላ ወንድ ሚስቱን ልክ… — አሳፍ Tube — TG.ME

Part 3 ምናልባት አንድ ልዩ ምሳሌ ልዩነቱን እንድንረዳ ያስችለናል፡፡ አንድ ባል ሌላ ወንድ ሚስቱን ልክ ባልሆነ መንገድ እንደወደዳት ካወቀ ለመቅናት መብት አለው፤ ይህ ዓይነቱ ቅንዓት ኃጢአት አይደለም፤ ይልቁንም ሙሉ በሙሉ ተገቢ ነው፡፡ አምላክ ለአንተ ነው ባለው ነገር መቅናት ተገቢ ነው፡፡ በገላትያ 5፡20 ላይ እንዳለው “ቅናት” የእኛ ያልሆነውን ነገር መፈለግ መመኘት ነው፡፡ አምልኮ፣ ምስጋና፣ ክብር እና ውዳሴ የእርሱ ብቻ ነው ምክንያቱም እርሱ አምላክ ስለሆነ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር አምልኮ፣ ምስጋና፣ ክብር ለጣዖታት ሲሰጥ ቀናተኛ ነው፡፡ ይህም ሐዋርያው ጳውሎስ በ2 ኛ ቆሮንቶስ 11፡2 ውስጥ የገለጠው ዓይነት ቅንዓት ነው “በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁ…“። የእግዚአብሔር ቀናተኛነት ከምን የመነጨ ነው? “እግዚአብሔር እነዚህን ቃሎች ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ ፤ ከግብጽ ከባርነት ምድር ያወጣሁህ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ።” በዘፀአት 20፡1-2 (አመት) ፤ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጣም ታዋቂ የሆኑት የእስራኤል ህዝብ በግብፅ ባርነት ውስጥ ሆነው ሳለ እግዚአብሔር ሙሴን ተጠቅሞ በድንቅ ትዓምራት አውጥቷቸዋል። እንዲሁም ደግሞ በምድረ በዳ ሲራቡ እያበላ፤ ሲጠሙ እያጠጣ፤ ልብስም ጫማም ሳይቸግራችው አምላካቸው ሆኖ እየመራ፤ እየጠበቃቸው፤ “አምላካችሁ እኔ ነኝ፤ ከኔ ሌላ አምላክ አታመልኩ” ብሎ በዘፀአት 20፡5 ሲያዛቸው እንመለከታለን። እስራኤላዊያን ከባርነት አለም ከወጡ በኋላ ግን ሙሴ በተራራው ላይ ሳይወርድ ለብዙ ጊዜ ሲቆይ ሕዝቡ አሮንን “…ናና በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ያ ከግብጽ ያወጣን ሙሴ ምን እንዳገኘው አናውቅም አሉት።” ዘፀአት 32፡1 (አመት) አሮንም ሕዝቡ እንድሚፈልጉት አድርጎ የወርቅ ጥጃ ሰራላቸው። ከዛም እነርሱ “…እስራኤል ሆይ፤ ከግብጽ ያወጡህ አማልክት እነዚህ ናቸው” ዘፀአት 32፡4 (አመት) እያሉ መስገድ እና ማምለክ ጀመሩ። ከግብፅ ምድር ያወጣቸው ሙሴ ሳይሆን እግዚአብሔር መሆኑን ዘንግተው በራሳቸው ጌጥ የተሰራ ጣዖትን አመለኩ። ለዚህም እግዚአብሔር በድጋሜ በዘፀአት 34፡14 ላይ “…ስሙ ቀናተኛ የሆነው እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ነውና ሌላ አምላክ አታምልኩ።” (አመት) ይላቸዋል። ስለዚም እግዚአብሔር የርሱ ያልሆን ነገር የሚፈልግ ሳይሆን፤ የሚገባውን የሚፈልግ ቀናተኛ አምላክ ስለሆነ ከእርሱ ወጪ አምልኮ እንድናቀርብ ፈቃዱ አይደለም። በሕይወታችን ውስጥ የእግዚአብሔርን ቀናተኛነት መረዳት እግዚአብሔር በህይወታችን ውስጥ ያደረገውን፣ የሰራልንን ስራ ስናስብ ምን ይሰማናል? እንደሚገባው እየኖርን ነውን? እግዚአብሔር በህይወታችን ያደረገውን ነገር ብናስብ ቆጥረን አንጨርሰውም፡፡ ከምንም የሚበልጠው ደግሞ አንድ ልጁን ክርስቶስን ለሰው ልጆች ዕዳ ከፍሎ ፤ከራሱ ጋር ያስታርቀን ዘንድ ወደ ምድር ላከው። ይሄም ተገብቶን ሳይሆን እንዲሁ ከፍቅሩ የተነሳ ነው፤ መፅሐፍ እንደሚል “በርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወድዷልና።“ ዮሐንስ 3:16 (አመት)። ታዲያ ዛሬ እያመለክን ያለነው ማንን ነው? በህይወታችን አብልጠን ጊዜ የምንሰጠው ለማን ነው? ስራ ስጠን ብለን እንዳልፀለይን ሲመልስልን ከቤቱ እንርቃለንን? ቸገረን ብለን አልቅሰን ሲሞላልን ከፊቱ እየጎደልን ይሆን? እግዚአብሔር በቃሉ የሚለን ትላንትናን ያሻገርኳችሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ ከኔ ሌላ ጊዜ የምትሰጡት፣ የምትገዙለት ነገር አይኑራችሁ፣ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቀናተኛ ነኝና።

❤2
July 18, 2026 124