በሳዑዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን መካከል በተፈጠረ ግጭት የተያዙ ሰዎች ጉዳይ በሕግ እየተመራ መሆኑን ኢምባሲው ገለጸ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 27 ቀን 2018 ዓ.ም (#አዲስ_ማለዳ)
በሳዑዲ አረቢያ በተለያዩ የማህበረሰብ ቡድኖች መካከል በተፈጠረ ግጭትና ግድያ ዙሪያ ከ100 በላይ ሰዎች በሕግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን በሪያድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቋል ።
ኤምባሲው እንደገለጸው ከሆነ በሳዑዲ አረቢያ ድንበር አካባቢና በበረሃማ አካባቢዎች በተፈጸመው ግጭትና ግድያ ተያይዞ ከሚሰራጩ የማህበራዊ ሚዲያ መረጃ ጋር በተያያዘ ኤምባሲው ከሳዑዲ የጸጥታ አካላት ጋር በቅርበት ሲከታተል እንደቆየ ገልጿል ።
በማህበረሰቡ እና በጸጥታ አካላት በኩል ለኤምባሲው በተሰጡ መረጃዎች መሠረት፣ በጥቃቱ የተሳተፉ አንድ ዋና ተጠርጣሪና አምስት ሌሎች ግለሰቦች ጨምሮ በሕግ ቁጥጥር ስር እንደዋሉ አስታውቋል።
በተጨማሪም፣ በማህበራዊ ሚዲያ ግጭትን ሊያባብሱ የሚችሉ መረጃዎችን በማሰራጨት የተጠረጠሩ ከ100 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የገለፀ ሲሆን ጉዳያቸውም በአሁኑ ወቅት በምርመራ ላይ መሆኑን ኤምባሲው ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
ኤምባሲው ከሳዑዲ የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር በጥቃቱ የተሳተፉ ሰዎች በሕግ ፊት እንዲቀርቡና የሕግ የበላይነት እንዲከበር እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል።
በመጨረሻም ኤምባሲው በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያልተረጋገጡ መረጃዎችን በማህበራዊ ሚዲያ እንዳያሰራጩ ጥሪ በማቅረብ በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃ ያላቸውም ለኤምባሲው እንዲያሳውቁ ጠይቋል።
ኤምባሲው በተጨማሪም ዜጎች የሳዑዲ አረቢያን ሕግና ደንብ እንዲያከብሩ፣ የራሳቸውንና የማህበረሰቡን ሰላም እንዲጠብቁ አሳስቧል።
ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
Twitter ➲ t.ly/mxA
1
1September 2, 2026 2.7K 4