የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ለስድስት ወራት ታግዶ የቆየውን የሮይተርስ ዘጋቢዎች ፈቃድ አደሰ
ዓርብ፣ ነሐሴ 22 ቀን 2018 ዓ.ም (#አዲስ_ማለዳ)
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከዓለም አቀፉ የዜና ተቋም ሮይተርስ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ከተወያየ በኋላ፣ ላለፉት ስድስት ወራት ታግዶ የቆየውን የሦስት ቋሚ የዜና ወኪሎቹን የዘገባ ፈቃድ ማደሱን አስታወቀ።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኃይማኖት ዘለቀ ከሮይተርስ ኤክስክዩቲቭ ኤዲተር ኒክ ታተር እና የአፍሪካ ኤዲተር ሲልቪያ አሎይሲ ጋር ባካሄዱት ውይይት፤ ተቋሙ ባለፉት ሰባት ወራት ካሰራጫቸው ዘገባዎች መካከል የተወሰኑት የኢትዮጵያን ሕግ፣ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅን እና ብሔራዊ ጥቅም የሚጻረሩ እንዲሁም የጋዜጠኝነት ሙያዊ ሥነ-ምግባርን ያልተከተሉ እንደነበሩ የሚዲያ ሞኒተሪንግ ውጤቶችን በማስደገፍ ማስረዳታቸውን የባለስልጣኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም፣ ሮይተርስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያሰራጫቸው አንዳንዶቹ ዘገባዎች በሚዛናዊነት፣ በትክክለኝነት እና በተአማኒነት በኩል ክፍተት የነበረባቸውና ወደ አንድ ወገን ያደሉ እንደነበሩ ገልጸው፣ ለተስተዋሉት የሕግና የሙያ ሥነ-ምግባር ጥሰቶች አስፈላጊው እርማት ሊደረግላቸው እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
በውይይቱ ላይ የሮይተርስ ኃላፊዎች በበኩላቸው፣ የዜና ወኪሉ ገለልተኛ ሚዲያ መሆኑን ገልጸው ዘገባዎችን ሚዛናዊ፣ በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሠረቱ እና ከአድልዎ የጸዱ ለማድረግ ጥብቅ የኤዲቶሪያል መመሪያዎችን እንደሚከተሉ አስረድተዋል። አያይዘውም አልፎ አልፎ ለተፈጠሩ ስህተቶች ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን አስፈላጊውን እርማት እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል።
ሮይተርስ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ክብር እንዳለው የገለጹት የሥራ ኃላፊዎቹ፣ ሀገሪቱ ባላት የሕዝብ ቁጥርና የኢኮኖሚ ግዝፈት ልክ ሰፊ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ሽፋን ማግኘት አለባት በሚለው አቋማቸው እንደሚጸኑ ተናግረዋል።
አክለውም የሀገሪቱን ሕግ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ እሴቶች በማክበር ዘገባዎችን እንደሚያቀርቡ እና ጋዜጠኞቻቸውም ብሔራዊ ጥቅምን ተረድተው የሙያ ሥነ-ምግባርን ጠብቀው እንዲሠሩ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
በውይይቱ ማጠናቀቂያ ላይ ከሕግና የሙያ ሥነ-ምግባር ጋር ተያይዞ ለጊዜው ታግዶ የቆየው የሮይተርስ የኢትዮጵያ የዜና ወኪሎች የዘገባ ፈቃድ እንዲታደስ በባለሥልጣኑ ተወስኗል።
በመጨረሻም ባለሥልጣኑ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ የሮይተርስ ቋሚ የዜና ወኪሎች ፈቃድ መታደሱን አውቀው አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉላቸው ጥሪ አቅርቧል።
ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
Twitter ➲ t.ly/mxA
Telegram
Addis Maleda - አዲስ ማለዳ
ዜና ከምንጩ

10
7August 28, 2026 4.8K 1 5