በኢንዶኔዥያ የተቀሰቀሰውን መንግስታዊ ተቃውሞና ሁከት ተከትሎ በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት ተስተጎጎለ… — Addis Maleda - አዲስ ማለዳ — TG.ME

Addis Maleda - አዲስ ማለዳPhoto
በኢንዶኔዥያ የተቀሰቀሰውን መንግስታዊ ተቃውሞና ሁከት ተከትሎ በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት ተስተጎጎለ

ዓርብ፣ ነሐሴ 22 ቀን 2018 ዓ.ም (#አዲስ_ማለዳ)

በኢንዶኔዥያ ዋና ከተማ ጃካርታ ተካሂዶ የነበረው ተቃውሞ ወደ ሁከት መቀየሩን ተከትሎ፣ የሀገሪቱ የትራንስፖርት ባለስልጣናት በዛሬው ዕለት አንዳንድ የባቡር እና የአውቶቡስ መስመሮች አገልግሎታቸውን እንዲያቋርጡ ወይም መስመር እንዲቀይሩ ማድረጋቸውን አስታወቁ።

በተለያዩ ቡድኖች አስተባባሪነት ትናንት ሐሙስ ጠዋት በፓርላማ ሕንጻ አቅራቢያ የተካሄደው ተቃውሞ፣ ባለፈው ዓመት ለሁለት ሳምንታት ዘልቆ የነበረውንና ለፕሬዝዳንት ፕራቦዎ ሱቢያንቶ አስተዳደር የመጀመሪያው ፈተና የሆነውን ከባድ ጸረ-መንግሥት ተቃውሞ ዓመት ታሳቢ ያደረገ እንደነበር ተገልጿል።

ሰልፈኞቹ በመንግሥት ፖሊሲዎች ላይ ያላቸውን ቅሬታ የገለጹ ሲሆን፣ በሙስና በተጠረጠሩ ባለስልጣናት ላይም ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።

ሰልፉ በዕለቱ ምሽቱን መበተኑ ቢገለጽም፣ ጥቁር ሸሚዝ የለበሱ ግለሰቦች ከሰልፉ በኋላ በጎዳናዎች ላይ በመቆየት የፖሊስ ጣቢያና ሁለት ሞተር ሳይክሎችን በእሳት ማቃጠላቸውን፣ መንገድ መዝጋታቸውን እንዲሁም በፖሊስ ላይ ድንጋይና ዱላ መወርወራቸውን የአካባቢው ሚዲያዎች ዘግበዋል።

ፖሊስ በበኩሉ ሁከቱን ለመበተን በአስለቃሽ ጭስ እና በከፍተኛ ጉልበት በሚረጭ ውሃ ምላሽ ሰጥቷል።

በአመጹ አካባቢ በርካታ የፍንዳታ ድምፆች የተሰሙ ሲሆን፣ የጃካርታ ፖሊስ እስካሁን በይፋ መግለጫ ባያወጣም የፖሊስ ቃል አቀባይ ቡዲ ሄርማንቶ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት አስተያየት የሁከት ድርጊቶች መከሰታቸውን አረጋግጠዋል። ፖሊስ ሁከት ለማስነሳት ሞክረዋል ያላቸውን 65 ሰዎችን ያሰረ ሲሆን፣ ከአስሪዎቹም ጋር የአየር ሽጉጦች፣ የመገናኛ መሣሪያዎች እና ሞሎቶቭ ኮክቴል ለመሥራት የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን መያዙን አስታውቋል።

የተቃውሞው መቀስቀስ እ.አ.አ. በ2024 በከፍተኛ ድምፅ ተመርጠው ወደ ሥልጣን የመጡት የቀድሞው ጄኔራል ፕሬዝዳንት ፕራቦዎ ሱቢያንቶ፣ በሕዝብና በባለሃብቶች ዘንድ እየተሸረሸረ የመጣውን እምነት ለመመለስ እየታገሉ ባሉበት አስቸጋሪ ወቅት ላይ የተከሰተ ነው። ቴምፖ በተሰኘው የምርመራ የዜና ድርጅት በቅርቡ በተካሄደ ጥናት የፕራቦዎ የሕዝብ ድጋፍ መጠን ወደ 38 በመቶ ዝቅ ማለቱ ታውቋል።

በሁከቱ ምክንያት በዛሬው ዕለት በጃካርታ የመንገደኞች ባቡር እና አውቶቡስ መስመሮች ላይ መስተጓጎል ያጋጠመ ሲሆን፣ በፓርላማው አቅራቢያ ያሉ በርካታ ዋና ዋና ጎዳናዎች መዘጋታቸውን የትራፊክ አስተዳደሩ መግለጹን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡


ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦

YouTube ➲ t.ly/vSgS
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
Twitter ➲ t.ly/mxA
Telegram
Addis Maleda - አዲስ ማለዳ
ዜና ከምንጩ
❤8
August 28, 2026 4.2K 4