“ጠላቶች በኢትዮጵያ ላይ የሸረቡትን ሴራ ለማክሸፍ የጸጥታ ኃይሉ ዝግጁ ነው” ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
ዓርብ፣ ነሐሴ 22 ቀን 2018 ዓ.ም (#አዲስ_ማለዳ)
የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጠላቶች ተቀናጅተው በኢትዮጵያ ላይ በርካታ ሴራዎችን በማቀድ ላይ እንደሚገኙ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
ኮሚሽነር ጄነራሉ ይህንን የገለጹት የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽነሮች እንዲሁም የሰላምና ጸጥታ ኃላፊዎች በተገኙበት ሀገራዊ የጋራ የጸጥታ መድረክ ላይ ነው።
በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፣ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ የጸጥታና አስተዳደር ኃላፊዎች፣ የሚሊሻ ኃይል እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት በተቀናጀ መልኩ በሠሩት ሥራ ትልቅ ሀገራዊ ድል ተመዝግቧል።
ከ50 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በሰላም ድምፁን እንዲሰጥ የጸጥታ ተቋማት ያከናወኑት ተግባር በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ አርአያ መሆን መቻሉን በመጥቀስ የምርጫውን ሂደት አሞካሽተዋል።
አያይዘውም የሀገር ውስጥና የውጭ ጠላቶች እንዲሁም “የውስጥ ባንዳዎች” ሲሉ የጠሯቸው አካላት ተቀናጅተው የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት ለማናጋት ሴራዎችን በማቀድ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። ነገር ግን የጸጥታ ኃይሉ እነዚህን አደገኛ እንቅስቃሴዎች ቀድሞ በማክሸፍ የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ሙሉ ዝግጅት ማድረጉን አረጋግጠዋል።
በመጨረሻም፣ ሀገሪቱ ጀምራዋለች ያሉት የዕድገት ጉዞ የተሳካ እንዲሆንና ሰላም እንዳይናጋ የጸጥታ አካላት ድርሻቸውን ከመወጣታቸውም በላይ፣ እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍልና ባለድርሻ አካል የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ጥሪ አቅርበዋል።
ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
Twitter ➲ t.ly/mxA
Telegram
Addis Maleda - አዲስ ማለዳ
ዜና ከምንጩ

6
5
2August 28, 2026 4K 11