RN.05 - Channel: post #4849 — TG.ME

🚩 ምክክር ወይንስ መምከን ?፦ የብልፅግና «አገራዊ ምክክር» ፈተናዎች እና የመዋቅራዊ ለውጥ አስፈላጊነት
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
ጡፌል ዘሃበሻ (ከመናገሻ)
.
መግቢያ
-------
ይህንን ጽሑፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝ በቅርቡ በብሔራዊ የምክክር ኮሚሽኑ መድረክ ላይ የተስተዋሉ አያሌ ጥያቄዎችን የሚያስነሱ ሂደቶች እና ድራማዊ ክስተቶች ናቸው።
1. ሰሞኑን የኮሚሽኑ ሰብሳቢ፦ "እዚህ አዳራሽ ዉስጥ የክልል ባለሥልጣናት፣ የከተማ ከንቲባዎች እና ሚንስትሮች አብረውን ሙሉ ቀን ይገኛሉ፤ ነገር ግን መገኘታቸው እንደ ማንኛውም ተመካካሪ በስነ-ስርዓት ቁጭ ብለው እንዲመካከሩ እንጂ ሥልጣናቸውን ወይንም ጉልበታቸዉን ሊያሳዩን አይደለም!..." ሲሉ ያደመጥናቸው ንግግር፣ የመድረኩን ነፃነት እና የባለሥልጣናቱን የፖለቲካ ተፅዕኖ በተመለከተ ከፍተኛ ሥጋት እንዲፈጠር አድርጓል።
.
2. አጀንዳ በተያዘበት የሙስሊሙ መብት ጉዳይ ላይ በሙስሊም ስም የተሳተፉ የብልፅግና አፈ-ቀላጤ የሰጡትን ተጻራሪ አስተያየት ስንመለከትም፦ "ለመሆኑ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ይህንን መድረክ እውነተኛ የውይይት መድረክ አድርጎ ቆጥሮታልን? የተሳተፉትስ አንዳንድ ተወካዮች የጠቅላላውን ማኅበረሰብ እውነተኛ ድምፅ ያንፀባርቃሉ ወይስ የመንግሥት ምርጫዎች ናቸው?" የሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን እንድንሰነዝር ያደርገናል።
.
3. በሌላ በኩል ደግሞ፣ መድረኩ ላይ ከተሳተፉት ሌሎች ማህበረሰቦች አንጻር ጥቂት የሚባሉ የተወሰኑ ሙስሊሞች ጥያቄዎቻቸዉን ይዘው በመድረኩ በመገኘታቸው ብቻ በሂደቱ ላይ ገንቢ ጥያቄ ከማንሳት ይልቅ፣ አጋጣሚውን ማኅበረሰቡን ለማጠልሸትና የጥላቻ ንግግሮችን ለማስፋፋት የተጠቀሙበትን በተለይ ጽንፈኛ "ጸረ ሙስሊም" ወገኖችን ዘመቻ ስንመለከት፣ የችግሩን መሠረታዊ ጉድለት በግልጽ ማስቀመጥ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
.
እውነተኛ የምክክር አስፈላጊነት፦
--------
ለዘመናት የተከማቹ መዋቅራዊ ስብራቶችን ለማቃናት፣ የታሪክ በደሎችን በሽግግር ፍትሕ ለመፈወስ እና የአገሪቱን የወደፊት ፖለቲካዊ ዕጣ-ፈንታ ለመወሰን እውነተኛ የብሔራዊ ምክክር መድረክ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አምናለሁ። የታሪክ ቁስል የሚድነው፣ የፍትሕ መጓደል የሚታረመው እና የዜጎች የባለቤትነት ጥያቄ እውነተኛ ምላሽ የሚያገኘው መላው የሀገሪቱ ሕዝቦችና ባለድርሻ አካላት በጋራ የዉይይት ማዕድ ዙሪያ ሲሰበሰቡና በአንድነት እና በልዩነታቸው ዙሪያ በግልጽና በነፃነት ሲወያዩ ብቻ ነው።
.
ሆኖም ግን አሁን እየተካሄደ ያለው ሂደት የምክክር ኮምሽነሩ እንዳሉት በባለሥልጣናት ጣልቃ-ገብነት እና በካድሬዎች አማካኝነት ይፋዊውን መስመሩን በመከላከል አዝማሚያ የተሞላ በመሆኑ፣ ከፍትሐዊና አካታች መድረክነት ይልቅ ቅቡልነትን ለማግኘትና ፖለቲካዊ አላማን ለማሳካት የሚደረግ ጥረት አስመስሎታል። ይህም፦ "ኢትዮጵያ እውነት እየመከረች ነው ወይስ በሂደቱ ምክንያት አገራዊ እድሏ እየመከነ ነው?" የሚል ጥልቅ ሥጋት እንድናነሳ ያስገድደናል።
.
ለዚህ ሥጋት ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፦
------------
1. የኮሚሽነሮቹ አሰያየም እና የገለልተኝነት ጥያቄ፦
የኮሚሽኑ የመጀመሪያውና መሠረታዊው ጉድለት የአወቃቀሩ ሁኔታ ነው። ኮሚሽነሮቹ የተመረጡበት ሂደት በገዢው ፓርቲ ቁጥጥር ሥር እንደዋለ የሚነሱት ቅሬታዎች ከፍተኛ ናቸው። ጎልተው የወጡ ዋና ዋና የፖለቲካ ተቃዋሚዎች፣ የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች እና ነፃ ምሁራን በበቂ ሁኔታ ከሂደቱ መገለላቸው፣ የመድረኩን ገለልተኝነትና ነፃነት ገና ከጅምሩ ጥያቄ ውስጥ ጥሎታል፤ ገለልተኝነት በጎደለበት ሁኔታ የሚደረግ «ብሔራዊ ምክክር» ደግሞ የሚጠበቀውን ዘላቂ ሰላም ማምጣት ይችላል ተብሎ አይጠበቅም።
.
2. የታሪክ ቁርሾዎችን ለፖለቲካ ጥቅም ማዋል፦
ለሕግ የበላይነትና ለፍትሕ በቂ ትኩረት በማይሰጥ ሥርዓት ውስጥ አገራዊ ችግሮችን በቅንነት ለመፍታት ያለው ቁርጠኝነት አጠራጣሪ ነው። ይልቁንም፣ ታሪካዊ ቁርሾዎችን አሁናዊ የፖለቲካ ጥንካሬ ማጠናከሪያ በማድረግ ሕዝብን ከሕዝብ፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት የማጋጨቱ አካሄድ አሁንም ድረስ የብዙ ዜጎችን ሕይወት ለህልፈት እየዳረገ ይገኛል። ልዩነቶችን ከመሠረቱ በቅንነት ከመፍታት ይልቅ ለጊዜያዊ ሥልጣን ማጽኛ የመጠቀም አዝማሚያ ባለበት ሁኔታ፣ ከዚህ ሂደት ዘላቂ አገራዊ መፍትሔ መጠበቅ እጅግ አስቸጋሪ ነው።
.
ይህንን እውነታ ይበልጥ የሚያጠናክረው ራሳቸው ጠ/ሚንስትሩ በመድረኩ መክፈቻ ላይ የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እና የፖለቲካ ኃይሎችን ያገለለ፣ አልፎም ማስፈራራት የተሞላበት ንግግር ማድረጋቸው ነው። ይህም የመድረኩን ጅማሮ እንኳን ቢያንስ በንግግራቸው ገለልተኛ እና ሁሉንም የሚያቅፍ ማድረግ እንዳልተቻለ የሚያሳይ ነው። ለዚህም ነው ሂደቱ የሕዝብ ውይይት ከመሆን ይልቅ የመንግሥትን ፍላጎትንና ፖለቲካዊ እቅድን ብቻ የሚያንፀባርቅ «የአንድ ወገን ትርኢት» ነው የሚሉ ትችቶች የበረቱበት።
.
3. የዋና ዋና ክልሎች እና ባለድርሻ አካላት አሳታፊነት ማነስ፦
ሌላው ጎልቶ የሚታየው መዋቅራዊ ጉድለት የአገሪቱን ፖለቲካዊ ዕድል በጋራ የሚቀርጹ የሚሰኙት የኦሮሚያ፣ የአማራ እና የትግራይ ክልሎች እውነተኛ እና ትርጉም ያለው ውክልና አለመኖሩ ነው። በነዚህ አካባቢዎች ሰፊ ግጭት እና ጥብቅ ፖለቲካዊ ውጥረት ባለበት ሁኔታ፣ መሬት ላይ ያለዉን እውነታ የሚያንፀባርቁ አካላት ሳይወከሉ በመንግሥት በተመረጡ ወገኖች ብቻ «ምክክር» ማካሄድ ሂደቱን ውጫዊና ተፅዕኖ የሌለው ያደርገዋል።
.
4. የጽንፈኛ አካላት ምላሽ እና የውክልና ክፍተቶች፦
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የተወሰኑ የሙስሊም ተወካዮች በመድረኩ በመገኘታቸው ብቻ፣ አጋጣሚውን በመጠቀም የሙስሊሙን ማኅበረሰቡን ለማጠልሸት የሚደረጉ የጽንፈኝነት እንቅስቃሴዎች እጅግ አሳሳቢ ሆነው ታይተዋል። እነዚህ እኩልነትን የማይሹ ጸረ ሙስሊም የሆኑ ጽንፈኛ ወገኖች አጠቃላይ ሂደቱን የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ፍላጎት ማስፈጸምያ አስመስለው ለማቅረብ እና የማህበረሰቡን መሠረታዊ ጥያቄዎችን ለማጣጣል ይሞክራሉ። ነገር ግን ሙስሊሙን ወክለዋል ተብለው የተሳተፉት አካላት ቁጥራቸው ከሌሎች አንጻር ሲታይ ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ ስፋት አንጻር እጅግ አነስተኛ ነው። ይህም ህዝበ ሙስሊሙ ለዘመናት ሲያነሳው የቆየውን ቁመቱን ያማከለ ተመጣጣኝና ፍትሐዊ የውክልና ጥያቄ ክፍተት የሚያሳይ እንጂ የማኅበረሰቡን እውነተኛ ፍላጎት የሚያስፈጽም በቂ ውክልና አይደለም።
❤6
August 8, 2026 595 1