ሀምሌ 4 በግፍ የተገደሉት ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ ሰማዕት የተባሉበትና ቀብራቸው በጎፋ ገብርኤል የተፈጸመበትን በማስመልከት የህይወት ታሪካቸውን ከያዘው መጽሐፍ የተቀነጨበ
..." አባታችን ምነው ደህና አይደሉም?"
"ጸጥ ብለው ከቆዩ በኋላ ሰዎች እየመጡ ከአገር ውጣ ወይም ሸፍት ይሉኛል። እኔ መነኩሴ ነኝ። እንግዲህ የመነኩሴ ሽፍታ ይታይህ -የመነኩሴ ሽፍታ። እኔስ አንገቴ ከብረት ላይ ተጋድሞ ከላይ ስለት እየወረደበት መሆኑ ይታየኛል። የምጠብቀው ስለቱ አንገቴ ላይ አርፎ አንገቴ ከአካሌ እስኪለይ ነው።" ገጽ 244
"... የእስር ቤት ኑሯቸው የቅዱስነታቸው አብዛኛው ጊዜአቸው በጾም በጸሎት በማስተማር የተጠመደ ነበር። ሌሊት ለተወሰነ ጊዜ ሲጸልዩ ያድራሉ። ጧትና ማታ በማኅበር ጸሎት ይካፈላሉ። አንዳንድ ጊዜም አጠር ያለ የማጽናኛ ምክር ይሰጣሉ። እሁድ እሁድ በንቡረዕድ ኤርምያስ ከበደ ረዳትነት ሥርዓተ ቅዳሴ ያደርሳሉ።..." ገጽ 280
" ... በሰሞነ ሕማማት እስረኞች ጧት ከሁለት እስከ ሰባት ሰዓት ይሰግዳሉ። ፓትርያርኩ ደሞ ከጧቱ ሁለት ሰዓት እስከ ሰባት ሰዓት አንድም ግዜ እንኳ ሳያቋርጡ ይሰግዳሉ።" ገጽ 282
ምንጭ ቀዳማዊ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ ከታምራት አበራ










