✍️ክርስትና ውትድርና ነው(ዶ/ር ማሙሻ ፋንታ)። በክርስትና ሕይወት ደስታም ሐዘንም ፣መውደቅም መነሳትም ፣መበርታትም መድከምም ያሉ የሕይወት ገጽታዎች ናቸው። ክርስትናን ከውትድርና ጋር ማነጻጸር ትክክለኛና ጥሩ ምሳሌ ነው። "እንደ ክርስቶስ በጎ ወታደር ሆነ ከእኛ ጋር መከራን ተቀበል"መጽሐፍ የሚለው ለዚያ ነው(2ኛ ጢሞ 2:3)። ውትድርና የረጅም ዓመት ሥልጠና ፣ትዕግሥት ፣ትጥቅ ፣የመከራ ሕይወት በመጨረሻም ማዕረግ ያለው የክብር ሕይወት የው። ወታደር የሚፈራው በማዕረጉ ልክ ነው። ከማዕረጉ ጀርባ ያለው የመከራ ሕይወት ፣ማዕረጉን በሚቀበልበት ጊዜ ከሚያገኘው ደስታ ጋር አይወዳደርም። ሴት የሚጧን ሕመምና ስቃይ ልጇን እንዳየች እንደምትረሳ ሁሉ ፣ወታደርም ማዕረጉን ስቀበል ያለፈውን መከራ ሁሉ ይረሳዋል።
የሐ.ሥራ 5:41 (NASV) ሐዋርያትም፣ ስለ ስሙ ውርደትን ለመቀበል በመብቃታቸው ደስ እያላቸው ከሸንጎው ወጥተው ሄዱ።
✍️የበጉ ሐዋርያትን ከሌሎች በጸሎት ከተጉ ጋር ፣ በመጀመሪያው ምዕተ ዓለም ከደረሰባቸው ችግርና መከራ የምንማረው ጠንካራ ትምህርት መካከል አንዱ በመከራ ውስጥ መደሰትን ነው። ሐዋርያት ጠንካራ አገልግሎት ወይም በክብር የታጀበን አገልግሎት እያገለገሉ ነው። በዚያውም ልክ ብርቱ መከራ ፣ዛቻና ስቃይ የበዛበት ሕይወት ነበራቸው። በሐዋርያት ሕይወት ውስጥ በስሙ መከበር ይቅርና ስለ ስሙ መዋረድ እንኳ የተገባቸው እንዳልሆኑ ራሳቸውን ማየታቸው ብርቱ መንፈሳዊነት ነው። በእግዚአብሔር ስም በኩል የሚመጣ ድል ፣ስኬት ፣ኃይል፣ብርታት ይቅርና ለስሙ የምንቀበለው መከራና ውርደት እንኳ የማይገባን ነን። በመከራው አክሊል አለን ፣በስደቱ መብዛት አለን ፣በዝቅታው ከፍታ አለን ለስሙ የምንቀበለው እያንዳንዱ ነገር ሽልማት አለው። ወዳጆቼ በርቱ እግዚአብሔር ይከፍላቸዋል።
✍️1ኛ የጴ 4:13 (NASV) ነገር ግን ክብሩ በሚገለጥበት ጊዜ ደስታችሁ ታላቅ እንዲሆን የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች በመሆናችሁ ደስ ይበላችሁ። ልጆች ከሆነን ወራሾች ደግሞ ነን፤ የክብሩ ተካፋዮች እንሆን ዘንድ በርግጥ የመከራው ተካፋዮች ብንሆን፣ የእግዚአብሔር ወራሾች፣ ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን(ሮሜ 8:17)። እግዚአብሔር ለመከራ ሕይወት ብቻ አልጠራንም ፣ለመከራ ሕይወትም አልጠራንም ፣ለታላቅ ደስታ ፣ ለዘለዓለም ሕይወት ያውም ፍጹም ፍስሐ ላለበት ሕይወት ተጠርተናል ነገር ግን በምድር ሕይወታችን ውስጥ በመከራ ሕይወት ልናልፍ እንችላለን። ከሰማዮ ሕይወታችን ደስታ አንጻር የምድሩ ሕይወታችን መከራ ምንም ነው። እግዚአብሔር ይመስገን አሜን(7*)። ለጌታ በመለየታችሁ ፣እሱ በእናንተ በመክበሩ ምክንያት መከራን ያገኛችሁ በሙሉ ታላቅ የደስታ ብድራት ከፊታችሁ አለ።
ወንድሞቼ ሆይ፤ ልዩ ልዩ መከራ ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት(ያዕ 1:2)
✍️Abuna
@EsayasAbuna
@Gospelofchristjesus