♦ የአማራ ሕዝብ ጠመንጃ የሚተኩሰው ነገረኛ ስለሆነ ነው እንዴ ?!
የዳንኤል ክብረት ዕዳ
ቀደም ባለው ጊዜ የቤተ ክህነት ከ 2010 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ የቤተ መንግስት "አማካሪና አዋቂ" የተደረገው ዳንኤል ክብረት መንግስታዊ የስድብ መጽሐፍ አስመርቋል። መጽሐፉ "የትርክት ዕዳ እና በረከት" ይሰኛል። ይህ የስድብ ሰነድ ቤተ መንግስት እራት በሚበሉና በሚያውደለድሉ የዘመኑ ተረኛ ሹማምንት ተመርቋል።
የመጽሐፉ መራቂና አድናቂ አለቃው ዐብይ አሕመድ ሲሆን "በአሁኑ አይነት እስከዛሬ መጽሐፍ አልጻፍክም ነበር" ሲል አሞካሽቶታል።ከመጽሐፉ ምርቃት በኋላም ማንነቱን እንደ እስስት በመቀያየር የሚታወቀው አቶ ዛድግ አብርሃ "የሞቱ ሰዎች ዕድል አግኝተው የዳንኤልን መጽሐፍ ቢያነቡት ምክሬ ነው "ሲል የማሽቃበጥን ክብረ ወሰን አሻሽሎታል።
ይህ የስድብና የአሉባልታ ሰነድ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በትርክት እንደተጎዳ ይገልጽና ኦነግ እና ህወሃትን በስማቸው ጠርቶ የትግል መነሻ እንዳላቸው ይገልጻል። የአገዛዙ አማካሪ ዳንኤል ክብረት ፤ የአማራን ብቸኛ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ኃይል ፋኖን ራሱ ባወጣው ስያሜ ጃውሳ ብሎ ከሰየመው ዋል አደር ብሏል።
እኔ እስር ላይ ብሆንም መጽሐፉን አንብቤ ጨርሻለሁ ። የዘር ፍጅት ንግግር በማድረግ የሚታወቀው ዳንኤል ክብረት ፤ የአማራን ሕዝብ ትግል በስድብ ጀምሮ በስድብ ጨርሶታል ። ግለሰቡ የአማራን ልጆች ጃውሳ እያለ ለመሳደብ 104 ገጾችን ተጠቅሟል ።
ዳንኤል ክብረት ህወሃትና ኦነግ የትግል መነሻ እንዳላቸው ይገልጽና የአማራ ሕዝብ ወኪል ፋኖ ግን ዘራፊና ወንበዴ እንደሆነና የትግል መነሻም እንደሌለውም ያትታል። የሱ አለቃ ዐቢይ አሕመድ ስልጣን ከያዘ በኋላ 17 ባንኮችን ስለዘረፈ አካል በመጽሐፉ ላይ አልተጠቀሰም።
የዚህ መጽሐፍ ደራሲ አለቆቹ እነ ለንጮ ለታ፣ እነ ጃዋር መሐመድ ፣ እነ ሽመልስ አብዲሳና አዳነች አቤቤ እንዳይከፉ በሚል አማሮች በወለጋ በተደጋጋሚ መጨፍጨፋቸውን አላነሳም ። ባንክን የሚያክል ተቋም ቀርቶ የአንድ ግለሰብን ክብር ያልነካውን የፋኖ ታጋይ ግን በዘራፊነት ፈርጇል። በመሰረቱ አማራ ለህልውናው ለመታገል ዳንኤልንና አለቆቹን ማስፈቀድ አይገባውም! አላደረገውም። አያደርገውምም።
ዳንኤል ክብረት ጃውሳ፣ ዘራፊና ወንበዴ የሚላቸው የአማራ ወጣቶችን ነው። የአማራ ሕዝብ ለፍቶ ያሳደጋቸው እና ከአብራኩ የወጡት ወጣቶች ጠበንጃ ያነሱት ጸብ አጫሪ ስለሆኑ ነው ?!
በሚሉዮን የሚቆጠር ወጣት መኖሪያ ቀዬውን ፣ እናት አባቱን፤ ሚስት ልጁን፤ ትምህርቱን ትቶ ጫካ የገባው ዝናብና ብርድ የተሻለ ምቾት ስላላቸው ነው ?! የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት የተገባ የሚሆነው "እየሱስን በአይኔ አየሁት፤ 10 ሚሊዮን ሕዝብ ሞቶ እኛ ሰላም ብንሆን፤ በሰው ልጅ አዕምሮ እንዳይታወሱ አድርጎ ማጥፋት ይገባል" ከሚል ግለሰብ ጋር አይደለም ።
ጸሐፊው ይህንን መጽሐፍ የጻፈው ከቤተ መንግስት ውዳሴና ግብዣ ላለመራቅ እንደሆነ ያነበበው ያውቀዋል። ሚሊዮኖች በይፋ የተሰደቡበት ይህ መጽሐፍ በዳንኤል ይጻፍ እንጅ ውስጡን የሞላው የኦሮሞ ብልጽግና የረጅም ጊዜ ዕቅድ ነው።
መጽሐፉ የአማራ ሕዝብን ትግል የሚያንቋሽሽና ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ አደገኛ ሰነድ ነው። በእርግጥ ሕዝቡ እንኳን ለራሱ ለሌሎች የሚተርፍ ብልህነት ስላለው በድሪቶ መጽሐፍ የሚጋጭ አይደለም። ፋሲል ግንብን ያነጸ ፤ ላሊበላን የፈለፈለ ሕዝብ ቤተ መንግስት ገብቶ የሚያደሸድሽ ግለሰብ ድሪቶ ሰነድ ስለጻፈ አጀንዳ አያደርገውም።
በአራቱም ግዛቶች በትጥቅ፤ በቀሪው የሀገሪቱ ክፍሎች ደግሞ በውስጥ አርበኝነት የአማራ ሕዝብ ለሕልውናው እያደረገ ያለውን የሞት ሽረት ትግል "የጥቂት ጽንፈኞች ነው" እያሉ ማቃጠር የማሰብ ችሎታ ድክመትን ያሳያል። የአማራ ሕዝብ ለምን እንደሚታገል ለዳንኤል አለቃ ማስረዳት የአማራ ሕዝብ ግደታ አይደለም ።
የአማራ ሕዝብ የሁልጊዜ ግደታ ህልውናውን ማስቀጠል ብቻ ነው። ዳንኤል ክብረት ቤተ መንግስት የሚወራውና ከኦሮሞ ብልጽግና ሰዎች የሚወጣውን ቃል እንደ እውነተኛ ማስረጃ የሚቆጥር የአራት ኪሎ አፋሽ አጎንባሽ ነው። በአንድ ወቅት "የህወሓት ሰዎች እንዳይታወሱ መደረግ አለበት" ካለ በኋላ የሚታወሱበትን ሽልማት ለራሳቸው ለህወሓት ሰዎች በእጁ የሰጠና ሰብዓዊ ክብሩን ካለምንም ገፊ ምክንያት እያራከሰ ያለ ግለሰብ ነው።
መላው የአማራ ሕዝብ ሆ ብሎ የተነሳበትን ትግል የትቢተኛ ጎረምሶች አድርጎ ለትውልዶች በሚቀመጥ መጽሐፍ ላይ ማስፈር የግለሰቡንም ሆነ የአለቆቹን የማሰብ አቅም ዝቅተኛ መሆን ያመለክታል።
የአማራን ሕዝብ ትግል አለመውደድ፣ ማውገዝ፣ መርገም እንዳይሳካ መመኘትም ይቻላል ። ይህንን ምኞት ግን እውነት ነው ብሎ በመጽሐፍ መደረትና ትንታኔ መስጠት ራስን፥ እንደማታለል ይቆጠራል። በተመሳሳይ የአማራን ፖለቲካዊና ወታደራዊ ኃይል ፋኖን መስደብና ያልሆነ ስም መስጠትም ይቻል ይሆናል ፤ እውነታውን መቀየር ግን አይቻልም፤ አልተቻለምም።
ፋኖ የሚንቀሳቀሰው በአማራ ሕዝብ ውስጥ ነው። የአማራ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ኃይል ፋኖ ከሕዝቡ ጋር ተባብሮና ተከባብሮ እየኖረ እየታገለ ሲሆን አብሮ አርሷል፤ አርሟል ፤ አዝመራ ሰብስቧል ። ይህን ታጋይ አንተ ባወጣከው ስም ጃውሳ አሊያም ወንበዴ ብትለው ቂም ከማትረፍና ታጋዩን ከማነሳሳት ውጭ እውነታውን መቀየር አይቻልም። የአማራን ታጋዮች የሚያውቃቸው የአማራ ሕዝብ ነው። አሳምነው ጽጌን ቢሮ ቁጭ ብሎ መሳደብ ይቻላል ፤ በአሳምነው ስም የሚምልና የሚታገል ሚሊዮን ወጣት እንዳለ መካድ ግን አይቻልም።
ዳንኤል ክብረት በመጽሐፉ ላይ የአሳምነው ጽጌ አስከሬን "ለምን በክብር ተቀበረ" ብሎ ጽፏል።
"አስከሬን ለምን በክብር አረፈ?" ብሎ መጽሐፍ የሚጽፍ የትኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ጤንነቱ ያጠራጥራል። አንድ ህሊና ያለው ሰው ጤንነቱ ካልታወከ አሊያም በጥላቻ ካልሰከረ በቀር፤ "አስከሬን በክብር ተቀበረ" ብሎ አየተበሳጨ መጽሐፍ ሊጽፍ አይችልም።
አዎ! አሳምነው ጽጌ በክብር አርፏል፤ በክብር ሽኝቱ ላይም በርካቶች ተገኝተዋል። ዕለቱም በየዓመቱ ይዘከራል። የመጽሐፉ ደራሲ ዳንኤል ክብረትን ምንም ልንረዳው አንችልም ፤ ምክያቱም አሳምነው በአካል ቢለይም ሚሊዮኖች በስሙ እየማሉ ነው። የአማራ ሕዝብ በአሳምነው ጽጌ ስም ብርጌድ ፣ ሻለቃ፣ ክፍለ ጦር ... አቋቁሟል።
ነገ ከነገወዲያ ከተሞች፣ ሞሎች፣ የባቡርና የአውሮፕላን ጣቢያዎች ፣ አውራጎዳናዎች፣ ኢንዱስትሪዎች በአሳምነው ጽጌ ስም ይሰየማሉ። ይህ በቅርቡ እንደሚሆን የስሜን ያህል እርግጠኛ ነኝ። ባህር ዳር ከተማ የሚገኘው በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንቦት 20 የሚል ስያሜ ነበረው፤ የአማራ ሕዝብ ባደረገው ትግል በአርበኛችን በላይ ዘለቀ ስም እንደተሰየመው ሁሉ ተቋሞቻችንን በአሳምነው ጽጌና በመሰል አርበኞቻችን የምንሰይምበት ጊዜ የቀረበ ነው።
በተመሳሳይ ዳንኤል ክብረት የዘመነ ካሴን ስም እየደጋገመ ጠቅሷል ። ዘመነንም በተመሳሳይ አለመውደድ ብቻ ሳይሆን መሳደብና መዝለፍ ይቻላል ፤ በዘመነ ካሴ ፤ አቅምና ችሎታ የአማራ ሕዝብ ላይበተን መሰባሰቡን መካድ ግን አይቻልም ።
3
3
2
1August 25, 2024 2.5K 1