ኤካ ኮተቢው አጠቃላይ ሆስፒታል በክረምት በጎ ፈቃድ መርሀ ግብር ከ200 ሺህ በላይ ዜጎችን ነፃ የሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚ አደረገ።
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም
በየካ ክፍለ ከተማ የሕክምና ወጪ መሸፈን ለሚቸገሩ በርካታ ነዋሪዎች እፎይታን ሲሰጥ የቆየውና ከ200 ሺህ በላይ ነፃ የሕክምና አገልግሎቶች የተሰጡበት የ11 ቀናት የበጎ ፈቃድ መርሃ-ግብር ዛሬ ተጠናቋል። በጤና ሚኒስቴር፣ በኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል እና በየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ትብብር የተዘጋጀው ይህ ነፃ የሕክምና አገልግሎት፣ የብዙዎችን የጤና ችግር በመቅረፍና ለዜጎች አስፈላጊውን የሕክምና ድጋፍ ተደራሽ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ተገልጿል።
በማጠናቀቂያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር የሜዲካል ሴንተሮች መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ኢሊባቡር ቡኖ እንደተናገሩት፣ በዘንድሮው ዓመት ብቻ በመላ ሀገሪቱ ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የዚህ ነፃ የሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናሉ። የኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር መገርሳ አለሙ በበኩላቸው፣ ባለፉት 11 ቀናት ለሕብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት በመቻሉ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፣ ለህክምናው መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ የጤና ባለሙያዎችና አጋር አካላት ምስጋና በማቅረብ መሰል ሰብዓዊ አገልግሎቶች ወደፊትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለሙ ኢምሮ፣ ላለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት የሕክምና ወጪ መሸፈን ለማይችሉ ወገኖች አገልግሎት ሲሰጥ ለቆየው ለኤካ ኮተቤ ሆስፒታልና ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል። በዚህ የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር ላይ እንደ ዋሽንግተን ሜዲካል ሴንተር፣ ላንሴት ሆስፒታል እና ጂአይቪ ሆስፒታል ያሉ የግል ተቋማትም በመሳተፍ የዜጎችን ህይወት ለመታደግ በተደረገው ጥረት ድጋፍ አድርገዋል ሲል የዘገበው የካ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ነው።
2July 25, 2026 308