በመዲናዋ በክረምት የበጎ ፈቃድ መርሀ ግብር 10 ሺህ በጎ ፈቃደኞች አገልግሎት በሚበዛባቸው የመንግስት ተቋማት ይሰማራሉ።
በከተማችን የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት በየጊዜው እያደጉ መምጣታቸውን የሚያሳይ "በጎነት በገልግሎት ሰጪ ተቋማት!" የተሰኘ የክረምት በጎ ፈቃድ መርሃ-ግብር ተጀምሯል። ዛሬ በተካሄደው መድረክ፣ አገልግሎት በሚበዛባቸው የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ውስጥ ተሰማርተው ህዝባቸውን የሚያገለግሉ በጎ ፈቃደኞች የስራ ስምሪት ተሰጥቷቸዋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ይመር ከበደ ለበጎ ፈቃደኞች የስራ መመሪያና አቅጣጫ ሰጥተዋል። ዋና ኮሚሽነሩ በንግግራቸው "በጎ ፈቃደኞች በሚሰማሩባቸው ተቋማት ሁሉ ዓለም አቀፍ የበጎ ፈቃድ መርሆዎችን በጥብቅ መከተል ይኖርባቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የአገልግሎት አሰጣጡን ውጤታማ ለማድረግ የተቋማቱን የአሰራር እሴቶችና ስነ-ምግባር አክብሮ መስራት ይገባል" ሲሉ አሳስበዋል።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ አስራት ንጉሴ በበኩላቸው፣ በከተማዋ የበጎነት ባህል እንዲዳብርና የህብረተሰቡ የጋራ እሴት እንዲሆን ባለፉት የለውጥ ዓመታት ዘርፈ ብዙና አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል። ይህ የዛሬው የስምሪት መርሃ-ግብርም የዚሁ ስኬታማ ጉዞ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
የበጎ ፈቃደኞቹን የስራ አካባቢ ምቹ የማድረግና የመደገፍን አስፈላጊነት ያነሱት ደግሞ በፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ የቢሮው አማካሪ አቶ አቡበክር ሀሽም ናቸው። አቶ አቡበክር በመንግስት ተቋማት ውስጥ ለሚሰማሩት ለእነዚህ በጎ ፈቃደኞች ተቋማቱ አስፈላጊውን ድጋፍና ቀጣይነት ያለው ክትትል እንደሚያደርጉላቸው አረጋግጠዋል።
ታዋቂው የስራ ፈጣሪና በጎ ፈቃደኛ ኢንጂነር ቢጄአይ ናይከር እና በመከላከያ ሰራዊትነት ለረዥም ጊዜ አገራቸውን ያገለገሉት 50 አለቃ ብርሃኑ አማረ በመድረኩ ተገኝተው ለበጎ ፈቃደኞቹ የረጅም ዘመን የስራ፣ የህይወትና የሀገር ፍቅር ልምዳቸውን አጋርተዋል።
ታዋቂ ግለሰቦች ያጋሩት ልምድና የተሰጣቸው የስራ አቅጣጫ ወደ አገልግሎት ከመግባታቸው በፊት የስነ-ልቦና ዝግጅት እንዲያደርጉ እንዳገዛቸውና መነሳሳት እንደፈጠረላቸው በጎ ፈቃደኞቹ ገልፀዋል።
ይህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በዜጎች መካከል የመረዳዳትና አብሮነትን የማጠናከር ትልቅ አገራዊ ፋይዳ ይኖረዋል።
3
2July 8, 2026 410