መንግሥት በቀጣይ 5 ዓመታት 1.5 ሚ.
ቤቶችን ለመገንባት ማቀዱ ተገለጸ
የዜጎችን የቤት አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ቢያንስ 1.5 ሚሊዮን አዳዲስ ቤቶችን ለመገንባት መዘጋጀቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ይፋ አደረጉ። ሀገሪቱ ባለፉት ሰባት ዓመታት 1.2 ሚሊዮን ቤቶችን መገንባቷን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አዲሱ ግዙፍ ዕቅድ በመንግሥት፣ በግል ዘርፉ እንዲሁም በመንግሥትና የግል አጋርነት (PPP) አማራጮች የሚተገበር መሆኑንና ለዚህ የሚረዳው ፖሊሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁን አብራርተዋል።
ይህንን ግንባታ በከተሞችም ሆነ በገጠር በከፍተኛ ፍጥነት ለማሳካት የ3D ቴክኖሎጂን ጨምሮ አዳዲስ የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂዎች፣ የሀገር ውስጥ ግብዓት አምራች ፋብሪካዎችና የሰለጠነ የሰው ኃይል በስፋት እየተዘጋጁ እንደሚገኙ ተጠቁሟል።
የቤት ግንባታው በተለይ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ሲሆን፣ የፋይናንስ አቅርቦቱን ለማመቻቸት መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው። ለዚህም ይረዳ ዘንድ ዜጎች ከሚያገኙት ገቢ ላይ እየቆጠቡ በረጅም ጊዜ ክፍያ የቤት ባለቤት የሚሆኑበት ዘመናዊ ሥርዓት እየተዘረጋ ሲሆን፣ ሙሉ በሙሉ መግዛት ለማይችሉ ወገኖች ደግሞ የመከራየት አማራጭ የሚቀርብበት አሠራር ይመቻቻል ተብሏል።
#ኢትዮጵያ #የቤትግንባታ #ዐቢይአሕመድ #የቤትልማት #ቴክኖሎጂ #Ethiopia #HousingProject #PMAbiyAhmed #3DPrinting #AffordableHousing
1July 7, 2026 285

