በአዲስ አበባ በክረምት የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር 2,500 ቤቶች ሊገነቡ ነው።
አዲስ አበባ| ሰኔ 15/2018 ዓ.ም፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአራዳ ክፍለ ከተማ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተጀመረው የቤት ግንባታና የአካባቢ ማደስ ፕሮጀክት፥ የመንግስትን ፖለቲካዊ ቃል ኪዳን ወደ መሬት የመቀየር ስትራቴጂ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል አሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ። ከንቲባዋ "የመረጠንን ህዝብ የምናመሰግነው በቃላት ሳይሆን በተግባራዊ ምላሽ ነው" ያሉ ሲሆን፥ ይህም ብልፅግና ፓርቲ በምርጫ ዳግም ኢትዮጵያን ለመምራት ተጨማሪ የአምስት ዓመት እምነት በተሰጠው ማግስት የተጀመረ መሆኑን ገልጸዋል።
በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በከተማ ደረጃ 2,500 ቤቶችን ለመገንባት የታቀደ ሲሆን፥ የዚሁ አካል የሆነውና ከከንቲባ ፅህፈት ቤት በስተጀርባ የሚገነባው የ“አራዳ የበጎነት መንደር” ግንባታ በይፋ ተጀምሯል። ይህ ሜጋ ፕሮጀክት ባለ 9 ወለል 8 ዘመናዊ የመኖሪያ ህንፃዎችን እና ባለ 4 ወለል ሁለት የገበያ ማዕከላትን ያካተተ ሲሆን፥ ለዘመናት የተጎሳቆሉ አካባቢዎችን በመቀየር ለሰው ልጆች ክብር የሚመጥን ዘመናዊ የጋራ መገልገያ፣ አረንጓዴ ስፍራና የስፖርት ሜዳዎችን ያካተተ መንደር እንደሚሆን ተገልጿል።
ከቤት ግንባታው በተጨማሪ በክረምት የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብሩ አካባቢን የማጽዳት፣ የጎርፍ መከላከያ ግንባታ፣ አቅም ለሌላቸው ማዕድ የማጋራት፣ የደም ልገሳ እና የነፃ ህክምና አገልግሎቶች እንደሚሰጡ ከንቲባዋ አስታውቀዋል። በተጨማሪም የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ፣ የተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እና የመንገድ ትራፊክ ማሳለጥ ስራዎችን በማከናወን ከተማዋን ለኑሮ ምቹ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቅሷል።
ለዚህ ታላቅ ግንባታ ስኬት የከተማዋ ባለሀብቶች ፈጣን ምላሽ የሰጡ ሲሆን፥ ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ በላይነህ ክንዴ እና ያደታ ጁነዲን እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ባለ 9 ወለል ህንፃ ለመገንባት ቃል ገብተዋል። በተመሳሳይ ቲኤንቲ ኮንስትራክሽን፣ ግራንድ ሌጋሲ ሃውስ፣ ኢቲ ኦንላይን፣ አብይ ማስረሻ፣ ዴማ ሪልስቴት፣ ቴምር ሪልስቴት፣ ስናፕ ትሬዲንግ፣ ጊፍት ሪልስቴት፣ መሃመድ አድናን እና አሚር በድሩ ቀሪዎቹን ህንፃዎች በጋራ ለመገንባት አጋርነታቸውን ማረጋገጣቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸው ምስጋና አቅርበዋል።
1June 22, 2026 210