የእውነት ዝናር የምንኖረው የተለያዩ እውነቶች እርስ በርሳቸው ተቻችለው በሚኖሩበት ዓለም ውስጥ ነው፡፡ እነዚህ የተለያዩ እውነቶች አንድ ላይ በመኖራቸው ምክንያት ሰዎች የተለያዩ እውነቶችን እየኖሩ ሁሉም እውነት ትክክል ነው ይላሉ። በግዜ ሂደት ውስጥ ደግሞ ይሄው ልማድ ወደ ቤተ-ክርስቲያን ገብቷል፡፡ ኢየሱስም አለው፦ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።(ዮሐንስ 14:6) በዚህ ክፍል ከተገለጸው በተቃራኒ የራሳችንን እውነት ስንኖር ትክክልና እውነት የሆነውን ክርስቶስን ትተን ለኛ የሚመቸንን ክርስቶስ እየተከተልን ነው፡፡ እንደ ክርስትያን ለምናምን ለእኛ አንድ እውነት ብቻ እንዳለ ነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረን፣ ያም እውነት የድነታችን መሰረት የሆነው ክርስቶስ ነው፡፡ ከራሱ ከኢየሱስ ውጪ ሌላ እውነት ቢኖር ኖሮ እራሱን ብቸኛው መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ ብሎ ባልጠራ ነበር፡፡ እውነት እግዚአብሔር የልጁን መልክ እንድንመስል እኛን የሚለውጥበት አንዱ የህይወት ስርዓት ነው፡፡ ከዚህ እውነት ጋር በማይስማማ መንገድ የምንኖር ከሆነ ደግሞ ራሳችንን ለጠላት ስራ አሳልፈን እንሰጣለን፡፡ በኤፌሶን 6 ላይ ስለ መንፈሳዊ ውግያ ሲናገር፣ የጠላትን ሀሳብ ለመቃወም ከምንጠቀማቸው የጦር እቃዎች አንዱ በወገባችን የምንታጠቀው የእውነት ዝናር ነው፡፡ በልካችን የተሰራ ቀበቶ በምናረግበት ግዜ ልብሳችንን በሚገባ እንደሚይዝልንና ምቾትን እንደሚሰጠን በተመሳሳይም የኢየሱስ ክርስቶስ እውነት በእኛ ውስጥ መኖሩ ዘላለማችን በክርስቶስ አማካኝነት የተጠበቀ እንደሆነ እያስታወሰ ከምንጠብቀው ተስፋ ጋር ይበልጥ ያጠብቀናል፡፡ በዚህም እውነት አማካኝነት ህይወታችንን እንቃኘዋለን፣ እንዲሁም ደግሞ አኗኗራችን ያለማቋረጥ ክርስቶስን ወደመምሰል እንዲያድግ እንተጋለን፡፡
4